Fana: At a Speed of Life!

የስምጥ ሸለቆዋ ንግስት፡ አዳማ

 

አዲስ አበባ፣ ጳጉሜን 5፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ጠዋት ፀሐይ ከአድማሱ ላይ ስትወጣ፣ የአዳማን ሰፊ ሰማይ በወርቃማ ብርሃን ታላብሰዋለች።

የገበያዎቿ የግርግር ድምፅ፣ የቡና ጭስ፣ የቅመም መዓዛና የሰዎቿ እንቅስቃሴ ተደራርበው የአዳማን የራሷን ልዩ ዜማ ይፈጥራሉ።

አዳማ በፀሐይ ሙቀት የደመቀች፣ በሰዎች እንቅስቃሴ የተሞላች፣ በባሕል የተሸለመች ከተማ ናት። በጎዳናዎቿ የሚጓዙ ሰዎች የተለያዩ ሕልሞችን ይዘው ይንቀሳቀሳሉ፡፡

በገበያዎቿ የሚሰሙ ድምፆችም የዕለት ተዕለት ሕይወቷን ይዘምራሉ። የሕዝቧ ፈገግታና እንግዳ ተቀባይነትም ከተማዋን ለመጣው ሰው ልብ የቀረበች እንድትሆን ያደርጋታል።

የዘመናዊቷ አዳማ ታሪክ ከ20ኛው መጀመሪያ ዘመን የባቡር ሐዲድ ልማት ጋር በጥብቅ ይያያዛል። ይህች የምስራቅ ፈርጥ አመሰራረቷ ከአዲስ አበባ-ጅቡቲ የባቡር መስመር መስፋፋት ጋር በጥብቅ የተቆራኘ እንደሆነ ታሪክ ያስረዳል፡፡

የባቡሩ እንቅስቃሴ አዳማን በቀስታ እያደገች እና እየሰፋች እንድትመጣ ምክንያት ሆነ፤አርሶ አደሮች፣ ነጋዴዎችና የባቡር ሠራተኞች በዙሪያዋ ተሰባሰቡ፤ መንገዶችና የንግድ ተቋማት ተከተሉ። በጊዜ ሒደትም አዳማ የመጓጓዣና የንግድ መገናኛ ማዕከልነቷን አጠናከረች።

ዛሬ ከተማዋ ከትናንቷ በእጅጉ ተለውጣለች። የከተማ አወቃቀሯ ተስፋፍቷል፤ የንግድና የኢንዱስትሪ ሚናዋ ጨምሯል፤ የመጓጓዣ አቅሟም ተጠናክሯል።

ከመዲናዋ አዲስ አበባ በቅርብ ርቀት ላይ መገኘቷ እና የዘመናዊው ፈጣን መንገድ ባለቤት መሆኗ ደግሞ አዳማን ለጉዞም ሆነ ለንግድ እንቅስቃሴ ተመራጭ አድርጓታል።

ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ የመጣው የመሰረተ ልማት ግንባታ እና የእንግዳ ተቀባይነት ባሕሏ ደግሞ «የስምጥ ሸለቆዋ እንቁ» የሚለውን መጠሪያዋን ፍጹም የተሟላ ያደርገዋል።

የአዳማ ቀጣይ ምዕራፍ ከከተማ ልማትና ኮሪደር ልማት ጋር እየተቆራኘ ነው። የኮሪደር ልማቱም መንገድ ብቻ ሳይሆን፣ የእግረኛ መስመር፣ አረንጓዴ ስፍራ፣ የሕዝብ መዝናኛ ቦታና ምቹ የከተማ አገልግሎትን በማስተሳሰር የከተማዋን ገጽታ ማሻሻል ላይ ትኩረት አድርጓል።

የመደመር መንግሥት እሳቤ የሆነው የኮሪደር ልማት አዳማ ከተማን ጽዱ፣ ምቹና ለኑሮ ተስማሚ እንዲሁም የተሳለጠ አገልግሎት የሚሰጥባት ከተማ እንድትሆን ጉልህ ሚና አበርክቷል፡፡

አዳማ ትናንት ባቡር ያነገሳት ከተማ ነበረች፤ ዛሬ ግን የመንገድ፣ የባቡር፣ የንግድና የኢንዱስትሪ መስመሮች የሚገናኙባት ትልቅ የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ ማዕከል ሆናለች።

የአዳማ ውበት በሕንፃና በመንገድ ብቻ አይለካም። የትናንት ታሪኳን ጠብቃ፣ የሕዝቦቿን ባህልና አኗኗር አክብራ፣ ከዘመኑ ጋር እየተራመደች መሆኗ ነው ልዩ የሚያደርጋት።

በአመለወርቅ ደምሰው

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.