Fana: At a Speed of Life!

የተለያዩ ሀገራት ኤምባሲዎች ለአዲስ ዓመት የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላለፉ

አዲስ አበባ፣ መስከረም 1፣ 2019 (ኤፍ ኤም ሲ) ተቀማጭነታቸውን በአዲስ አበባ ያደረጉ የተለያዩ ሀገራት ኤምባሲዎች፣ አምባሳደሮችና ዓለም አቀፍ ተቋማት ኃላፊዎች ለ2019 ዓ.ም አዲስ ዓመት የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።
በመጪው አዲስ ዓመት በኢትዮጵያ ሰላም፣ አንድነት እና ብልጽግና እንዲሰፍን እንዲሁም ከየሀገራቱ ጋር ያለው ግንኙነት ይበልጥ እንደሚጠናከር ያላቸውን እምነት ገልጸዋል።
በኢትዮጵያ የተባበሩት አረብ ኤሚሬቶች አምባሳደር አብደላ አል ሸምሲ ባስተላለፉት መልዕክት፤ አዲሱ ዓመት የሰላም፣ የፍቅር እና የልማት እንዲሆን ተመኝተዋል።
በኢትዮጵያ የማሌዥያ ኤምባሲ ጉዳይ አስፈጻሚ ሞህድ አፈንዲ አቡበከር በበኩላቸው፣ ለኢትዮጵያውያን እንኳን ለ2019 ዓ.ም አዲስ ዓመት አደረሳችሁ ብለዋል።
አዲሱ ዓመት ለኢትዮጵያ ሕዝብና መንግሥት የብልጽግና፣ የጤና እና የደስታ እንዲሁም መልካም ምኞታቸውን ገልጸዋል።
በኢትዮጵያ የስሪላንካ አምባሳደር ኒርማላ ኢንዱማቲ ዲያስ ፓራናቪታና በበኩላቸው፣ አዲሱ ዓመት ለኢትዮጵያ ሕዝብ አብሮነትና ብልጽግናን እንዲሁም ለተቋማቷ ጥንካሬን ይዞ እንዲመጣ ተመኝተዋል።
በኢትዮጵያ የጀርመን ተጠባባቂ አምባሳደር ፈርዲናንድ ቮን ዌይሄ አዲሱ ዓመት ለኢትዮጵያ የሰላም፣ የአንድነት እና ብልጽግና እንዲሆን ተመኝተዋል።
በፊንላንድ የኢትዮጵያ ኤምባሲ ምክትል ሚሲዮን መሪ ፒርጆ-ሊሳ ሄይኪላ አዲሱ ዓመት ለኢትዮጵያውያን የደስታ እና የብልጽግና እንዲሆን ተመኝተዋል።
በኢትዮጵያ የዴንማርክ ኤምባሲ ምክትል ሚሲዮን መሪ ሚርጃ ክሮኔ በአዲሱ የኢትዮጵያ ዓመት በሁለቱ ሀገራት መካከል ያለው የጸና አጋርነት የሚጠናከርበት እንዲሆን ተመኝተዋል።
በኢትዮጵያ የእስራኤል አምባሳደር አብርሃም ንጉሴ (ዶ/ር) መላው ኢትዮጵያዊያንን እንኳን ለአዲሱ ዓመት 2019 ዓ.ም አደረሳችሁ፤ አዲሱ ዓመት የሰላም፣ የእድገትና የፍቅር ዘመን እንዲሆንላችሁም ልባዊ ምኞቴን እገልጻለሁ ብለዋል።
የአውሮፓ ህብረት ከኢትዮጵያ ጋር ያለውን አጋርነት በአዲሱ ዓመት አጠናክሮ እንደሚቀጥል የገለጹት ደግሞ በኢትዮጵያ የአውሮፓ ህብረት አምባሳደር ሶፊ ፍሮም-ኤምስበርገር ናቸው።
አምባሳደር ሶፊ ፍሮም-ኤምስበርገር አገሪቷ ወደ 2019 ዓ.ም ስትሸጋገር ለኢትዮጵያውያን ብልፅግናና ደስታን ተመኝተዋል።
የተባበሩት መንግስታት የኢትዮጵያ ቢሮ አዲሱ ዓመት የሰላም፣ የደስታ እና የብልጽግና እንዲሆን መመኘታቸውን ኢዜአ ዘግቧል።
በኢትዮጵያ የአሜሪካ፣ የሩሲያ፣ የቻይና፣ የዩናይትድ ኪንግደም፣ የኢራን፣ የፓኪስታን፣የሜክሲኮ፣ የአውስትራሊያ እና የካናዳ ኤምባሲዎችም የአዲስ ዓመት የመልካም ምኞት መግለጫቸውን አስተላልፈዋል።
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.