Fana: At a Speed of Life!

ኢትዮጵያ አፍሪካን በተሻለ የሚረዳ የአርቴፊሻል ኢንተለጀንስ ዩኒቨርሲቲ እየገነባች ነው – ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር)

አዲስ አበባ፣ መስከረም 2፣ 2019 (ኤፍ ኤም ሲ)ኢትዮጵያ አፍሪካን በተሻለ የሚረዳ የአርቴፊሻል ኢንተለጀንስ ዩኒቨርሲቲ እየገነባች ነው አሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይህንን ያሉት በሕንድ ኒው ዴልሂ እየተካሄደ በሚገኘው በ18ኛው የብሪክስ መሪዎች  ጉባኤ ላይ ነው።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር) በጉባዔው ፥ ማናቸውም አይነት ዓለም አቀፋዊ ፈተናዎች እርስ በርሳቸው የተሳሰሩ በመሆናቸው ሀገራዊ ፅናትና ዝግጁነት አስቀድሞ መገንባት እንዳለበትና ይህም የመንግስታት ዋነኛ የአስተዳደር አካል ሊሆን እንደሚገባ  ተናግረዋል።

ኢትዮጵያም ይህንን ፅናት በተግባር በተለያዩ ዘርፎች  እያረጋገጠች  እንደምትገኝ አብራርተዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር) ፥ ኢትዮጵያ  ቀደም ሲል ከነበረችበት የስንዴ ምርት ጥገኝነት በመላቀቅ አሁን ላይ ራሷን መቻሏን አመልክተዋል።

በጤናው ዘርፍም ኢትዮጵያ የሀገር ውስጥ የመድኃኒት (ፋርማሲዩቲካል) ማኑፋክቸሪንግን በስፋት እያሳደገች ትገኛለች ነው ያሉት።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ  የዲጂታል መታወቂያ (Digital ID)፣ የክፍያ ስርአቶች እና የዳታ ልውውጥን ያካተተ የዲጂታል ህዝባዊ መሠረተ ልማት እየተገነባ መሆኑን ጠቅሰው ዳታዎች በአስተማማኝና በሕጋዊ መንገድ ጥቅም ላይ እንዲውሉ የሚያስችሉ ደንቦችም እየተተገበሩ ስለመሆናቸው አንስተዋል።

አፍሪካ የኤ አይ ትውልድ በመገንባት ረገድ የምርምር፣ የክህሎት እና የጠንካራ ተቋማት ባለቤት መሆን አለባት ብለዋል።

በዚህ ረገድም ኢትዮጵያ የአርቴፊሻል ኢንተለጀንስ ዩኒቨርሲቲ እየገነባች እንደሆነና ዩኒቨርስቲው አፍሪካን በተሻለ የሚረዳ የቴክኖሎጂ አቅም ለመገንባት ትልቅ አላማ ይዞ እየሰራ መሆኑን አስረድተዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ የብሪክስ ጥምረት ጥንካሬ እያንዳንዱ አባል ሀገር ይዞት በሚመጣው አቅም ላይ የተመሰረተ መሆኑን ጠቁመው አፍሪካ ለአረንጓዴ ኢነርጂ ሽግግርና ለዲጂታል ኢኮኖሚ እጅግ ወሳኝ የሆኑ የተፈጥሮ ማዕድናት ባለቤት መሆኗን አመልክተዋል።

በዚህም በጥምረቱ ውስጥ የሚገኘውን ካፒታል፣ ቴክኖሎጂ እና ገበያ ከአፍሪካ የተፈጥሮ ሀብት ጋር በማጣመር ማዕድናቱ በሚገኙበት ስፍራ ላይ የላቀ እሴት መፍጠር እንደሚገባ አስገንዝበዋል።

በሶስና አለማየሁ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.