ኢትዮጵያ በዓለም የጎዳና ላይ ሩጫ ሻምፒዮና 2ኛ ደረጃን ይዛ አጠናቀቀች
አዲስ አበባ፣ መስከረም 10፣ 2019 (ኤፍ ኤም ሲ) ኢትዮጵያ በዴንማርክ ኮፐንሃገን በተካሄደው ሁለተኛው የዓለም የጎዳና ላይ ሩጫ ሻምፒዮና ሁለተኛ ደረጃን ይዛ አጠናቅቃለች።
ለሁለት ቀናት ሲካሄድ የቆየው ሻምፒዮና ዛሬ ፍጻሜውን ያገኘ ሲሆን ÷ ከ86 ሀገራት የተወጣጡ ከ450 በላይ አትሌቶች ተሳትፈዋል።
ኢትዮጵያ በሻምፒዮናው ላይ በወንዶችና በሴቶች ግማሽ ማራቶን፣ በወንዶችና በሴቶች አምስት ኪሎ ሜትር እንዲሁም በሴቶች አንድ ማይል ውድድሮች ላይ ተሳትፋለች፡፡
በመርሐ ግብሩ ኢትዮጵያ በአንድ የወርቅ፣ ሁለት የብር እና አንድ የነሐስ በድምሩ አራት ሜዳሊያዎችን በማግኘት ሁለተኛ ደረጃን ይዛ አጠናቃለች።
ልቅና አምባው በአምስት ኪሎ ሜትር የወርቅ እና ፍሬወይኒ ኃይሉ በአንድ ማይል የብር ሜዳሊያ ለኢትዮጵያ አስገኝተዋል።
በተጨማሪም ኢትዮጵያ በቡድን በግማሽ ማራቶን ወንዶች የብር እና በግማሽ ማራቶን ሴቶች የነሐስ ሜዳሊያ አግኝታለች።
ኬንያ በሶስት የወርቅ፣ ሶስት የብር እና አንድ የነሐስ በአጠቃላይ ሰባት ሜዳሊያዎች በማግኘት ውድድሩን በበላይነት አጠናቅቃለች፡፡