ብሪክስ ይበልጥ ያጠነከረው የኢትዮ-ሩሲያ ወዳጅነት
አዲስ አበባ፣ መስከረም 8፣ 2019 (ኤፍ ኤም ሲ) ኢትዮጵያ በታኅሣሥ 22 ቀን 2016 ዓ.ም የብሪክስ ስብስብ ሙሉ አባል መሆኗ በሁለትዮሽና በብዝሃ ግንኙነቷ ላይ በርካታ በረከት ይዞላት መጥቷል።
ኢትዮጵያ በህንድ ኒው ዴልሂ ባለፈው ሳምንት የተስተናገደውን 18ኛውን የብሪክስ የመሪዎች ጉባኤን ጨምሮ በብሪክስ የተለያዩ መድረኮች ባደረገችው ተሳትፎ የተጀመረውን ሀገራዊ ዕድገትን የሚደግፉ ዕድሎችን ፈጥራለች።
የኢትዮጵያ የብሪክስን መቀላቀል ከፈጠራቸው ዕድሎች መካከል ሀገሪቱ ከሩሲያ ጋር ያላትን ታሪካዊና ስትራቴጂካዊ የሁለትዮሽ ግንኙነት ወደ ላቀ ሁለገብ ደረጃ ለማሸጋገር ትልቅ ተቋማዊ አቅም መፍጠሩ አንዱ ዕድል ነው።
እንደ ውጪ ጉዳይ ኢንስቲትዩት መረጃ፤ ከ1890 ዓ.ም የተጀመረው የኢትዮጵያና ሩሲያ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት በወዳጅነት ዘልቋል።
ይህንን የረጅም ጊዜ ወዳጅነት የብሪክስ ማዕቀፍ በከፍተኛ ሁኔታ አጎልብቶታል።
ሀገራቱ አጋርነታቸው ከተለመደው የሁለትዮሽ ግኑኝነት ባለፈ በዓለም አቀፍና ቀጣናዊ የኢኮኖሚ ትብብር ማዕቀፍ ውስጥ እንዲቃኝ አድርጎታል።
ብሪክስ የሁለትዮሽ ዲፕሎማሲን ከመተካት ይልቅ የተቋማዊ ግኑኝነቶችን በማብዛት የሀገራቱን መሪዎችና ከፍተኛ ባለሥልጣናት በየጊዜው እንዲገናኙ፣ በጋራ ጉዳዮች ላይ እንዲመክሩና ውሳኔዎችን እንዲያስተላለፉ ሰፊ ዕድል ፈጥሮላቸዋል።
በዚህ የትብብር ማዕቀፍ አማካኝነት በኢትዮጵያና በሩሲያ መካከል ያለው የንግድ፣ የኢንቨስትመንት፣ የደኅንነትና የቴክኖሎጂ ግንኙነት የሚጨበጡ ውጤቶችን እያሳየ ይገኛል።
ለአብነት ያህል በ2017 ዓ.ም በሁለቱ ሀገራት መካከል ያለው የሁለትዮሽ የንግድ ልውውጥ ከሦስት እጥፍ በላይ በማደግ ከ435 ሚሊየን ዶላር በላይ ደርሷል።
በዚህም ሩሲያ ወደ ኢትዮጵያ የአፈር ማዳበሪያ፣ የግብርና ማሽነሪዎች፣ የኃይል ማመንጫ መሳሪያዎችን ጨምሮ የተለያዩ ምርቶችን ልካለች።
በተጨማሪም በሰላማዊ የኒውክሌር ኃይል ልማት መስክ የተደረጉ የትብብር ስምምነቶች የሀገራቱን የግንኙነት ጥልቀት ያሳያሉ፤ እነዚህ ንግድን፣ የግብርና ማሽነሪዎችንና የኒውክሌር ቴክኖሎጂ ሽግግርን ያካተቱ እንቅስቃሴዎች የኢትዮጵያን የረጅም ጊዜ የኢነርጂ ዋስትናና የሀገር ውስጥ የቴክኒክ አቅም ለማሳደግ ጉልህ አስተዋጽኦ አላቸው።
በተመሳሳይ ሁኔታ የብሪክስ መድረክ ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ የኢኮኖሚና የፋይናንስ ሥርዓት ማሻሻያ ውይይቶች ላይ ድምጻን ለማሰማትና ከሩሲያ ጋር በባለብዙ ወገን ዲፕሎማሲ የተቀናጀ አቋም ለመያዝ አቅም ሰጥቷታል።
ከዚህም ባሻገር የኢትዮጵያ የብሪክስ ተሳትፎ የሀገሪቱን ስትራቴጂካዊ ነፃነት ሳይነካ የውጭ ግንኙነቷን እንድታስፋፋና ብሔራዊ ጥቅሟን እንድታስከብር ያስችላታል።
በመሆኑም የብሪክስ አባልነት የኢትዮጵያ እና ሩሲያን ታሪካዊ ወዳጅነት ወደ ዘመናዊ፣ ውጤታማና የጋራ ዕድገትን የሚያረጋግጥ ቁልፍ አጋርነት ለመቀየር እንደ ዋና የትብብር መድረክ ሆኖ እያገለገለ ይገኛል።
በአብረሃም አበራ