የአዲሱ መንግሥት ምስረታ ሥነ ሥርዓት መስከረም 25 ይካሄዳል – አፈ ጉባዔ ታገሰ ጫፎ
አዲስ አበባ፣ መስከረም 13፣ 2019 (ኤፍ ኤም ሲ) መስከረም 25 ቀን 2019 ዓ.ም የአዲሱ መንግሥት ምሥረታ እና የምክር ቤቱ መክፈቻ ሥነ ሥርዓት ይካሄዳል አሉ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባዔ ታገሰ ጫፎ፡፡
አፈ ጉባዔ ታገሰ ጉዳዩን አስመልክተው ባስተላለፉት መልዕክት ÷7ኛው ጠቅላላ ምርጫ 42 የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ 10 ሺህ 438 ዕጩዎች እንዲሁም ከ54 ሚሊየን በላይ መራጮች ተሳትፈው በስኬት መጠናቀቁን አስታውሰዋል፡፡
ጠቅላላ ምርጫው ሰላማዊ፣ ዴሞክራሲያዊ፣ ፍትሃዊና ተዓማኒነት ባለው ሁኔታ በስኬት መከናወኑንም ነው የገለጹት፡፡
በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 50 ንዑስ አንቀጽ 3 መሠረት የፌዴራሉ መንግሥት ከፍተኛ የሥልጣን አካል የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መሆኑንና ተጠሪነቱም ለኢትዮጵያ ሕዝብ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡
የምክር ቤቱ የሥራ ዘመንም በመስከረም ወር የመጨረሻ ሳምንት ሰኞ እንደሚጀምር በሕገ-መንግሥቱ አንቀጽ 58 ንዑስ አንቀጽ 2 ተደንግጓል ነው ያሉት፡፡
በተጨማሪም በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 56 መሠረት በምክር ቤቱ አብላጫ መቀመጫ ያገኘ የፖለቲካ ድርጅት ወይም ጣምራ ድርጅቶች የፌዴራሉን መንግሥት የሕግ አስፈጻሚ አካል እንደሚያደራጅና እንደሚመራ ጠቁመዋል፡፡
በዚህ መሰረትም መስከረም 25 ቀን 2019 ዓ.ም የአዲሱ መንግሥት ምሥረታ እና የምክር ቤቱ መክፈቻ ሥነ ሥርዓት እንደሚከናወን አስታውቀዋል፡፡
አፈ ጉባዔው ለመርሐ ግብሩ አስፈላጊ ዝግጅቶች ሙሉ በሙሉ ተጠናቅቀዋል ማለታቸውንም የምክር ቤቱ መረጃ ያመላክታል፡፡