Fana: At a Speed of Life!

ኢትዮጵያ ዓባይ ወንዝን ለማልማት የማንንም ይሁንታ አትጠይቅም – አምባሳደር ዘሪሁን አበበ

አዲስ አበባ፣ መስከረም 13፣ 2019 (ኤፍ ኤም ሲ) ኢትዮጵያ የዓባይ ወንዝን ጨምሮ ሌሎች ወንዞቿን አልምታ ለመጠቀም የማንንም ይሁንታ አትጠይቅም አሉ በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የአፍሪካ ጉዳዮች ዳይሬክተር ጄነራል አምባሳደር ዘሪሁን አበበ፡፡
አምባሳደር ዘሪሁን አበበ እንዳሉት፤ ግብጽ በዓባይ ወንዝ ላይ ማስቀጠል የምትሻው የቅኝ ግዛት ፍላጎት ላይመለስ አክትሟል፡፡
ኢትዮጵያ ወንዞቿን አልምታ ለመጠቀም የማንንም ይሁንታ አትሻም ሲሉ ተናግረዋል።
በኢትዮጵያውያን ደምና ላብ የተገነባው ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ የተፋሰሱ ሀገራት በውሃ ሀብታቸው ፍትሃዊ ተጠቃሚ እንዲሆኑ አዲስ ምዕራፍ የከፈተ የልማት ፕሮጀክት መሆኑንም ጠቁመዋል።
ይህም የግብጽን ወንዙን በብቸኝነት የመቆጣጠር የብቸኝነት ዘመን ማብቃቱን ማሳያ ነው ብለዋል፡፡
በቀጣይም በዓባይና በገባር ወንዞች ላይ የታችኛውን ተፋሰስ ሀገራት የማይጎዱ ነገር ግን የኢትዮጵያን የመልማት መሻትና ብሔረዊ ጥቅም የሚያስጠበቁ የልማት ፕሮጀክቶች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ ጠቁመዋል፡፡
በወንዞቿ ላይ የሚገነቡት የኃይል ማመንጫና የመስኖ ግድብ ፕሮጀክቶች የኢትዮጵያን የልማት ፍላጎት ከማሟላት ባለፈ፤ ቀጣናዊ ትስስርንና የጋራ ተጠቃሚነትን ለማጠናከር ጉልህ ፋይዳ እንዳላቸው ገልጸዋል።
ግብጽ ደካማ የውሃ አስተዳደር ያላትና ውሃ አባካኝ ሀገር መሆኗን አንስተው፤ የአስዋን ግድብ በበረሃማ አካባቢ መገንባቱ ከፍተኛ የውሃ ትነትን በማስከተል ከፍተኛ የውሃ ብክነት እንዲከሰት እያደረገ ነው ብለዋል፡፡
በዚህም ከ14 እስከ 16 ቢሊየን ሜትር ኩብ የሚጠጋ ውሃ እያባከነች መሆኑንም አመልክተዋል፡፡
በአንጻሩ ሕዳሴ ግድብ የውሃ ሀብትን በተቀናጀ ሙያዊ የውሃ አስተዳደር የሚመራና ያለምንም ብክነት ለኢትዮጵያና ለሌሎች የተፋሰሱ ሀገራት የልማት እድል የሚፈጥር መሆኑን ጠቁመዋል።
ግብጽ የምታራምደው የቅኝ ግዛት ዘመን እሳቤ የላይኛው ተፋሰስ ሀገራትን በተፈጥሮ ሀብታቸው የመልማት መብታቸውን እንዳይጠቀሙ አስሮ ማቆየቱን ጠቅሰዋል።
በ21ኛው ክፍለ ዘመን ይህ አካሄድ እንደማይሰራ ገልጸው፤ የግብጽ ሰሞናዊ ለቅሶ የዓለም አቀፍ የውሃ ሕግን ካለማወቅ የመነጨና መቼም የማይመለሰውን በብቸኝነት የመጠቀም አካሄድን የማስቀጠል ከንቱ ጥረት ነው ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡
ግብጽ የዓባይ ወንዝ ተቀባይ ሀገር እንደመሆኗ በትብብር መስራት ብቸኛ አማራጯ መሆኑንም አስገንዝበዋል።
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.