የመቐለ ከተማ ከንቲባ ሺሻይ አማረ (ዶ/ር) ከከተማዋ የንግድ ማህበረሰብ ጋር ተወያዩ
አዲስ አበባ፣ ሕዳር 6፣ 2019 (ኤፍ ኤም ሲ) በትግራይ ክልል ባለአደራ አስተዳደር የመቐለ ከተማ ከንቲባ ሺሻይ አማረ (ዶ/ር) ከከተማዋ የንግድ ማህረሰብ ጋር ተወያይተዋል፡፡
በውይይት መድረኩ በከተማዋ ተግባራዊ ለማድረግ የታቀደው የኮሪደር ልማት ፕሮጀክት ለኢኮኖሚ ዕድገት የሚኖረውን አስተዋጽኦ፣ የሚፈጥራቸውን የንግድና ኢንቨስትመንት ዕድሎች እንዲሁም የንግድ ማህበረሰቡን ተሳትፎ ለማጠናከር ያለመ ምክክር ተደርጓል፡፡
የኮሪደር ልማት ፕሮጀክቱ የመቐለ ከተማን ገጽታ ከማሻሻል ባለፈ ዘመናዊ መሠረተ ልማት በመገንባት ለንግድ ሥራ ምቹ ሁኔታ ለመፍጠር፣ የቱሪዝም መስህብነቷን ለማሳደግና አዳዲስ የኢንቨስትመንት ዕድሎችን ለመፍጠር እንደሚያስችል ተነስቷል፡፡
የንግድ ማህበረሰቡ በከተማዋ የልማት ሂደት ውስጥ ያለው ሚና፣ ከመንግሥት ተቋማትና ከፕሮጀክቱ አስፈጻሚ አካላት ጋር በትብብር መሥራት የሚያስፈልግበት ሁኔታ እንዲሁም የአተገባበር ሂደቱን በተመለከተ ውይይት ተደርጓል፡፡
በተለይም ፕሮጀክቱ የታሰበውን ውጤት እንዲያስገኝ የግሉ ዘርፍ ንቁ ተሳትፎ፣ የባለሀብቶችና የነጋዴዎች ትብብር እንዲሁም በሁሉም ባለድርሻ አካላት መካከል የጋራ መግባባት መፍጠር ወሳኝ መሆኑ አጽንኦት ተሰጥቶበታል።
የኮሪደር ልማቱ በከተማዋ አዳዲስ የሥራ ዕድሎችን ከመፍጠርና የንግድ እንቅስቃሴን ከማነቃቃት ባለፈ፣ የከተማዋን ኢኮኖሚያዊ አቅም በማጠናከር ዘላቂ ዕድገት ለማረጋገጥ የሚኖረው ፋይዳም በመድረኩ ተዳሷል።
በተጨማሪም ፕሮጀክቱ ከተማዋን ዘመናዊ፣ የንግድና የኢንቨስትመንት ማዕከል ለማድረግ ከተያዘው ዕቅድ አንጻር የንግድ ማህበረሰቡ ተሳትፎና ቀጣይነት ያለው ትብብር ወሳኝ መሆኑ ተጠቁሟል።
በግዛቸው ግርማዬ