Fana: At a Speed of Life!

ባዳም ተደነቀ፤ ባንዳም ተሸማቀቀ

ሁለቱ ስፍራዎች የሀገር ስምና መልክ ናቸው!
የዘመናዊት ኢትዮጵያን በተለይ ደግሞ የዚህን ትውልድ የሐሳብ፣ የተግባር እና የውጤት ተምሳሌት ሆነው ለዓለም የሚመሰክሩ ጉባና ቢሾፍቱ። ምሥራቅ እና ምዕራብ፤ የብርሃን መውጫም የብርሃን ማደሪያም።
በጉባ ተራሮች ሥር ጳጉሜን 4 ቀን 2017 ዓ.ም የተካሄደውን የታሪክ እጥፋት የኢትዮጵያ ወይም የኢትዮጵያዊ ብቻ አይደለም፡፡ የጥቁርነት እና የነጻነት መንፈስን የሚጋራ የዓለም ሕዝብ ሁሉ የማይዘነጋው፤ የሚዘክረው ታሪካዊ ቀን ነው።
“እንዴት?” ካላችሁኝ፣ ምክንያቴ ይህ ነው።
የባርባዶስ ጠቅላይ ሚኒስትር ሚያ ሞትሊ ለታዋቂው ኮሜዲያን ትሬቨር ኖዋ በእልህ እና በቁጭት፣ ነገር ግን ድልን በሚያበስር መልኩ እጃቸውን በስሜት እያወናጨፉ የተናገሩትን ከቶ ማን ሊረሳው ይችላል?
“ዓለም እምቢኝ ባለበት ወቅት፤ እነሱ አደረጉት! 14 ዓመታትን ፈጅቶባቸዋል፤ ግን አደረጉት!” (They did it when the World said no. It took 14 years. BUT, THEY DID IT!)
ከዚህ ሌላ ስሜቱ እንዴት ሊገለጽ ይችላል!
ያቺ የዓለም ጉራማይሌ የታሪክ መታያ ሆና የኖረች ሀገር፤ በአንድ በኩል የዘመናዊ ሥልጣኔ መነሻ እና የነጻነት ቀንዲል፣ ወዲህ ደግሞ የአንድ ዘመን ክፉ ረሃብ ስሟን ተጣብቷት የኖረች ክብርት እመቤት፤ ዓለም ግራ በተጋባ መነጽር የሚያያት ኢትዮጵያ የቀድሞ ሥልጣኔዋን የሚያሳይ፣ የአፍሪካ መግቢያ በር መሆኗን የሚመሰክር የዚህ ዘመን አዲስ ማንነት፣ ደግሞም የዚህ ዘመን የሀገር መሪዎች ጥበብ ጎልቶ አዲስ ታሪኳ እንግዲህ መጻፍ ጀመረ።
የኢትዮጵያ ዘመን ቆጠራ በሕዳሴው ብርሃን ለሁለት ተከፈለ።
የምዕራቡ የጸሐይ ማደሪያ የሕዳሴ ግድብ ብስራት ለምሥራቁ ነጸብራቁ ደረሰና መሪዋ ከሀገሪቱ ምዕራብ ጫፍ ከጉባ ተራሮች ሥር ቆሞ፣ በምሥራቅ የሚደገም ሌላ የዚህ ዘመንን ከፍታ አበሰረ!
የአህጉሪቱ ግዙፍ አውሮፕላን ማረፊያ ሐሳብ እነሆ ወደሚታይ ተግባር ተለውጦ፣ የምታጓጓ ሀገርን ለትውልድ የመሥራት ውጤትተሰናስሎ ቀጠለ።
ይኸው ሌላ የባዳ መደነቅ፤ የአቪዬሽን ጉዳዮችን እየተከታተለ በመጻፍ የሚታወቀው “አቪየሽን ዊክ” በሰራው መጠነኛ ዳሰሳ፣ በቅርብ ዓመታት ውስጥ ከተጀመሩ የአቪዬሽን ዘርፍ ፕሮጀክቶች እንደ ቢሾፍቱ አየር ማረፊያ ታላላቅ ዓለም አቀፍ ሚዲያዎችን ቀልብ ሰብስቦ የወሰደ ጉዳይ እንደሌለ ቁጥሮችን ምስክሬ ብሎ በየዘርፉ አስቀምጦ ተንትኖታል።
የምዕራቡ የሕዳሴ ጮራ ወደ ምሥራቅ የብርሃን ጸዳሉን አስፍቶ፣ ኢትዮጵያን ከጉባ ሥር በተወለደ አዲስ ብስራት እነሆ ስሟን በዓለም አደባባይ ወደሚገባው ክብር እያሻገረ ቀጥሏል።
ይህ ከፍታ የሩቅ የሆኑ የኢትዮጵያ ባዳዎችን ሲያስደንቅ፣ በነ “ለሞንድ” እና በነ “ኤንታይ ኤሮ” የሕትመት ገጾች በኩል ደግሞ የሀገር ውስጥ ባንዳው በሀገር ስኬት መኩራት ሲገባው፣ በተቃራኒው አፍሮ ሲሸማቀቅ ታይቷል።
ምሥራቅም ምዕራብም የባዳ መደነቅንና የባንዳ መሸማቀቅን እየታዘቡ፣ የኢትዮጵያን አዲስ ቀን በአዲስ ገጽ እየጻፉ ሰሜኑንም ደቡቡንም በብርሃናቸው ጸዳል የማዳረስ ጉዞአቸውን ተያይዘውታል።
በነቢዩ ይርጋለም
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.