Fana: At a Speed of Life!

ትዝታ ሸከተፍ ፣ ከአዲስ አበባ እስከ ጅቡቲ

አዲስ አበባ፣ መስከረም 14፣ 2019 (ኤፍ ኤም ሲ) መጀመሪያ ድምፁ ከሩቅ ይሰማል። ቀጥሎ የብረት እግሮቹ በብረት ሀዲድ ላይ የሚፈጥረው ምት፣ ልብን የሚያንኳኳ ስርአት ያለው ትርታ ይሆናል። ጭሱ ገና ሳይታይ ሽታው ይቀድማል፣ የነዳጅ ሽታ ከውጨው አየር ጋር ተቀላቅሎ፣ የባህርና የብረት ፍትጊያ የፈጠረው ልዩ ጠረን።

ሸከተፍ…. ሸከተፍ…. ሸከተፍ…. ሸከተፍ….

ይህ ድምፅ በድሬዳዋም ሆነ በጂቡቲ ጣቢያ ለአንድ ምዕተ ዓመት ገደማ ሲደጋገም ኖሯል። ዛሬም ይደገማል፤ ድምፁ ተቀይሯል፣ ታሪኩ ግን አልተለወጠም።

እስቲ ወደዚያ ትዝታ እንመለስ

ድሬዳዋ የተወለደችው ከባቡር ሀዲድ ላይ ነው ማለት ይቻላል። ከመቶ ዓመታት በፊት፣ ባቡሩ ገና ምድሯን ሲነካካ፣ ምንም ያልነበረበት ስፍራ ላይ ህይወት መጉረፍ ጀመረ።

ነጋዴዎች መጡ፣ ሰራተኞች ተከተሉ፡፡ ከአፋር፣ ከሶማሌ፣ ከኦሮሞ፣ ከአማራ፣ ከሐረሪ… እንዲሁም ከውጭ ሀገራት የተውጣጡ ሰዎች በአንድ የባቡር ጣቢያ ዙሪያ ተሰበሰቡ።

ቋንቋዎች ተቀላቀሉ፤ ምግቦች ተዋሃዱ፤ የካፌዎች ጠረጴዛ ላይ የፈረንሳይኛና የአፋርኛ፣ የሶማልኛና የአማርኛ ንግግር በአንድ ጊዜ ይሰማ ነበር። ድሬዳዋ የተገነባችው በጡብ ብቻ ሳይሆን፣ በእነዚህ የተቀላቀሉ ድምፆች ነው።

ግን ባቡሩ ይህን ብቻ አላደረገም።

ባቡሩ የመለያየትም ምልክት ሆኖ ኖሯል። ትናንት፣ ወጣቶች ወደ ጂቡቲና ወደ ውጭ ዓለም ህልም ተሸክመው ሲወጡ፣ ባቡሩ “የብረት እባብ” ተብሎ ይጠራ ነበር::

በጣቢያው ላይ የስንብት እንባና የመመለስ ደስታ በአንድ ላይ ይታዩ ነበር፤ እናቶች ልጆቻቸውን እጃቸውን እያውለበለቡ ሲሸኙ፣ ተመላሾችን ደግሞ ጨርቅ እያውለበለቡ ሲቀበሉ ይታይ ነበር።

የኢትዮጵያ ሙዚቃ ባቡሩን ፈጽሞ ችላ አላለውም። ባቡር በብዙ ዘፈኖች ውስጥ የፍቅርና የናፍቆት መልእክተኛ ሆኖ ተገልጿል፤ አንዳንድ ጊዜ የተወደደውን ሰው የሚወስድ ጨካኝ ገጸ ባህሪ፣ ሌላ ጊዜ ደግሞ ተስፋን የተሸከመ ወዳጅ ሆኖ ይሳላል።

በዘፈኖች ውስጥ ባቡሩ ብዙ ጊዜ አካልና ነብስ ያለው ይመስል ይነገርለታል፤ የፍቅረኛን መልእክት የሚያደርስ፣ የናፍቆት ደብዳቤ የሚሸከምተደርጎ ይሳላል።

” እልም አለ ባቡሩ እልም አለ ባቡሩ… እልም አለ…” የሚሉ ተደጋጋሚ ግጥሞች በአድማጭ ልብ ውስጥ ተቀርፀው ቀርተዋል፤ ያ ምት፣ ያ ድግግሞሽ፣ ራሱ የባቡሩን እግር ትርታ የሚመስል ዜማ ፈጥሯል። ሙዚቃና ብረት ተዋህደው አንድ ትዝታ ሆነዋል።

ባቡሩ ትዝታ ብቻ አይደለም። ከጂቡቲ ወደብ ተጭነው በባቡር ወደ ኢትዮጵያ የሚገቡት እቃዎች፣ ለሀገሪቱ ወሳኝ ናቸው። የጨውና የባህር አየር ጠረን፣ በኮንቴይነሮች ውስጥ ታሽጎ፣ በባቡሩ መስመር አድርጎ ወደ መሀል ሀገር ይገባል፡፡

የድሮው ባቡር ቀስ ብሎ ይጓዝ ነበር፤ እንፋሎት እየተነፈሰ፣ ጭስ እየተፋ። ያ ባቡር የፈረንሳይ የእጅ ስራ ውጤት ነበር፡፡ መንገደኞች በመስኮት ተደግፈው፣ ከውጭ የሚያልፈውን ገጠር እየተመለከቱ፣ ከልባቸው ጋር ይነጋገሩ ነበር።

ዛሬ ግን የኢትዮ- ጂቡቲ ምድር ባቡር በኤሌክትሪክ ኃይል ይጓዛል፤ ፈጣን፣ ዘመናዊ፣ ጸጥተኛ ነው። ጭስ የለውም፣ የድንጋይ ከሰል ሽታም የለውም።

ፍጥነቱ የዘመን መልክ ይመስላል፡፡ ሁሉም ነገር ቶሎ የሚደረግበት፣ ጊዜ የማይጠበቅበት ዘመን ላይ ባቡሩም ልክ እንደዘመኑ ይፈጥናል፡፡ በየቀኑ የኢትዮጵያን ሎጂስቲክስ ያፋጥናል፡፡

ትናንት ባቡሩ ናፍቆትንና ትዝታን ይሸከም እንደነበረ ሁሉ፣ ዛሬም ባቡሩ ተስፋንና ትስስርን ይይዛል። ትናንት የፍቅረኛሞችን ደብዳቤ ይዞ ይጓዝ የነበረው ባቡር፣ ዛሬ የሁለት ሀገራት ህልምና ንግድ ተሸክሞ ይጓዛል። በሀዲዱ ላይ የሚጓዘው ህልም ግን ከትውልድ ወደ ትውልድ ተላልፏል።

ሸከተፍ…. ሸከተፍ….

እዚያ ተመሳሳይ ሀዲድ፣ ትናንት የናፍቆት እንባ የፈሰሰበት ቦታ ላይ፣ ዛሬ አዲስ ትውልድ ወደ ስራው፣ ወደ ትምህርቱ፣ ወደ ህልሙ ይጓዛል። ባቡሩ ግን ታሪኩን አልረሳም። እያንዳንዱ ጉዞ፣ ትናንት የተጓዙትን ሁሉ ትዝታ ተሸክሞ ከተፍ ይላል ፡፡

ትናንትም ዛሬም፣ በጭስም ሆነ በኤሌክትሪክ፣ በተስፋ ድሬዳዋና ጂቡቲ በዚያ ብረት ሀዲድ የተሳሰሩ ናቸው። ባቡሩ ገና ይጓዛል፡፡ የሁለት ህዝቦችን ትዝታና ህልም ተሸክሞ ይጓዛል ፣ ወደፊት፣ ወደፊት፣ ወደፊት።

ሸከተፍ…. ሸከተፍ….

በአፈወርቅ እያዩ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.