ደመራ የሕብረ ብሔራዊነት ውብ መልክ
አዲስ አበባ፣ መስከረም 16፣ 2019 (ኤፍ ኤም ሲ) በየዓመቱ መስከረም 16 ቀን በኢትዮጵያ በተለያዩ አካባቢዎች የመስቀል ደመራ በድምቀት ይከበራል፡፡
የደመራ በዓል በሀገሪቱ በአደባባይ በድምቀት ከሚከበሩ ዋና ዋና በዓላት አንዱ ነው፡፡ የበዓሉ አከባበር ኢየሱስ ክርስቶስ የተሰቀለበት እውነተኛ መስቀል መገኘቱን ከማሰብ ባሻገር በሕዝቦች መካከል ሰላምን፣ ፍቅርንና አንድነትን በማጠናከር በኩልም ትልቅ የአብሮነት እሴት ነው።
በዓሉ ለዘመናት የኢትዮጵያውያን ማኅበራዊ አንድነትና ጥንካሬ መሠረት ሆኖ አገልግሏል። የደመራ በዓል የዘር፣ የብሔር፣ የቋንቋም ሆነ የሃይማኖት ልዩነቶችን የሚሻገር ነው።
በበዓሉ ወቅት ማኅበረሰቡ አለመግባባቶችን ለመፍታት፣ ማኅበራዊ ግንኙነቶችን ለማደስ እና የጋራ እሴቶችን ለማጠናከር አጋጣሚውን ይጠቀማል።
በከተሞችም ሆነ በገጠር መንደሮች ሕዝቡ በመሰል በዓላት በአንድነት በመሰብሰብ ማኅበራዊ ትስስሩን ማጠናከሩ የሀገሪቱ የጋራ ማንነት መገለጫዎች መሆናቸውን ያመላክታል።
በዓሉ የኢትዮጵያን የሃይማኖት ሀገርነት፣ የበለፀገ ማኅበራዊ ባህል፣ ዘመናትን የተሻገሩ ወጎችን እና የቆየ የእንግዳ ተቀባይነት እሴትን ለዓለም ማሳየቱ በማይዳሰሱ የዓለም ቅርስነት አስመዝግቦታል።
የበዓሉ ሃይማኖታዊና ባህላዊ ሥነ ሥርዓቶች፣ ዝማሬዎችና ያማሩ ሃይማኖታዊ እንዲሁም ባህላዊ አልባሳት ኢትዮጵያ ለዓለም አቀፍ ማኅበረሰብ የምታቀርበውን ውብ ባህል ያጎላሉ።
በዚህም ምክንያት በዓሉ በየዓመቱ በርካታ የውጭ ሀገር ጎብኚዎችን ይስባል። በኢትዮጵያውያን ልዩ የእንግዳ ተቀባይነትና ማራኪ ባህል የሚደመሙት እነዚህ ጎብኚዎች፣ የሀገሪቱን ሌሎች ታሪካዊና ተፈጥሯዊ ስፍራዎች ለመጎብኘት በኢትዮጵያ የሚያደርጉትን ቆይታ ያራዝማሉ።
በተፈጥሮና ባህላዊ ሃብቶች የታደለችዋ ሀገር ኢትዮጵያ በዓላቷም የዚህ ተፈጥሯዊና ባህላዊ ውህደት ማረጋገጫ ናቸው።
የታላቋ ሀገር ኢትዮጵያ ሕዝቦች እነዚህን ሥነ ሥርዓቶች ማኅበራዊ ሕይወትን፣ ፍቅርንና ሰላምን ለማጠናከር ለዘመናት ሲጠቀሙበት ኖረዋል፡፡
የደመራው ብርሃን ምሽቱን ሲያበራ በዓሉ ሃይማኖታዊ ክዋኔ ብቻ ሳይሆን የኢትዮጵያውያን የአንድነትና የፍቅር መገለጫ መሆኑን የእያንዳንዱ ታዳሚ ገጽታ ይመሰክራል፡፡
በምሕረት ደምሴ