የኢትዮጵያ ጥንካሬና የግብፅ ዋጋ ቢስ የተንኮል ካርዶች
አዲስ አበባ፣ መስከረም 24፣ 2019 (ኤፍ ኤም ሲ) ግብፅ የኢትዮጵያን ልማት እና ሰላም አጥብቀው ከማይሹ ሀገራት ግንባር ቀደሟ ናት፡፡ ግብፅ የኢትዮጵያ ታሪካዊ ጠላት የሚያስብላት በርካታ ምክንያቶች አሉ።
በታሪክ ወደ ኋላ መለስ ብለን ብንመረምር ኢትዮጵያ ላይ የተነሱ የህልውና ፈተናዎች ሁሉም በሚባል ደረጃ የግብፅ የስውርና ግልፅ እጆች አሉባቸው፡፡
በአሳፋሪ ሽንፈት የተጠናቀቀው የጉንደት እና ጉራዕ የቀቢጸ ተስፋ ወረራ እስከ የሀገር ውስጥ ገንጣይ አስገንጣይ ቡድኖች ወታደራዊ፣ ዲፕሎማሲያዊና የፕሮፓጋንዳ ድጋፍ መስጠት የግብፅ ለዘመናት የዘለቁ ፀረ-ኢትዮጵያ ተግባራት ናቸው፡፡
አሁንም በአባይ ወንዝ እና ተፋሰስ ላይ ልማት እንዳታከናውን በሚል ኋላቀር አስተሳሰብ በኢትዮጵያ ውስጥ ነፍጥ ያነሱ ባንዳዎችን ደግፋ ሰላሟን ለማናጋትና ልማቷን ለማደናቀፍ አበክራ እየሠራች ትገኛለች፡፡
ለልማት ዋነኛ ቅድመ ሁኔታ ሰላም፣ መረጋጋትና አንድነት መሆኑ ይታወቃል፡፡ ኢትዮጵያዊያን በትብብር በመሥራትና ኢኮኖሚያቸውን ለማሳደግና ሰላማቸውን ለማፅናት የሚያደርጉትን ጥረት ለማደናቀፍ ግብፅ ያልቆፈረችው ጉድጓድ የለም፡፡
ግብፅ በቀጣናው ያላትን ቁጥር አንድ ተሰሚ የመሆን ፍላጎቷን ለማሳካት ራሷን አንዳንዴ እንደ አረብ፣ ሌላ ጊዜ ደግሞ እንደ አፍሪካዊ ሀገር መልኳን እየለዋወጠች በሁለት እግር ሁለት ዛፍ ላይ ለመውጣት ትፍጨረጨራለች፡፡
ኢትዮጵያ በተፈጥሮ ሀብት አጠቃቀም ላይ ያላትን የጋራ ተጠቃሚነትና አብሮ የማደግ መርህ በመቃወም “ሁሉ የኔ” የሚል የራስ ወዳድነት አካሄድ የግብፅ መለያ ባህሪዋ ከሆነ ዘመናትን ተሻግሯል፡፡
ኢትዮጵያ አባይን ለመገደብ የፋይናንስ ድጋፍ እንዳታገኝ ከማስተጓጎል ጀምሮ አሳማኝነት የሌለው የስጋት ጥያቄ በማንሳት ኢትዮጵያ በሌሎች ሀገራት ዘንድ እንደ ክፉ የተፋሰስሱ ሀገር እንድትታይና በቀጣናው ያላት ተሰሚነት እንዲቀንስ በርካታ ዓለም አቀፋዊ እና ቀጣናዊ ጥረቶችን ስታደርግ ቆይታለች ፡፡ ሁሉም የካይሮ መፍጨርጨሮችና ጥረቶች በኢትዮጵያ ብልሃት የተሞላበት ዲፕሎማሲያዊ አካሄድ እና በልጆቿ አንድነት ከሽፈዋል፡፡
ኢትዮጵያ የባሕር በር ያጣችበት ታሪካዊ ኢፍትሐዊ ክስተት በቀጥታ እና በተዘዋዋሪ መንገድ የግብፅ ሚና ከፍተኛ እንደነበር ሀገር ያወቀው ፀሐይ የሞቀው ሀቅ ነው፡፡
የግብፅ የሁል ጊዜም ጥረት ኢትዮጵያ በቀጣናው ጠንካራ እና በልማት የተራመደች ሀገር ሆና እንዳትታይ ማድረግ ነው፡፡ ይህን ለማሳካት ታዲያ የውስጥ ባንዳዎችን በመጠቀም ግጭቶችን በመጥመቅ እና ልማቷ እንዲደናቀፍ የማድረግ ቀቢጸ ተስፋ ሙከራ ዛሬም ድረስ እንደቀጠለ ነው፡፡
ኢትዮጵያ የግብፅን በርካታ ሴራዎች ተቋቁማ በራሷ አቅም አባይን ከመገደቧ ባሻገር የባሕር በር ባለቤትነት ጥያቄዋን ማንሳቷ ሙሉ ጊዜዋን የኢትዮጵያን ልማት ማስተጓጎል ላይ ለምታውለው ግብፅ ትልቅ ጭንቀት ፈጥሮባታል።
ግብፅና አጋሮቿ የሚያደርጉት ፀረ-ልማትና ፀረ-ሰላም እንቅስቃሴ ከኢትዮጵያ ባለፈ የቀጣናውን ሰላም የሚረብሽ፣ በጋራ የመሥራትን መርህ የሚጥስና የመተማመንን መንፈስ የሚሸረሽር በመሆኑ ኢትዮጵያዊያን፣ የቀጣናው ሀገራትና ዓለም አቀፍ ማኅበረሰብ ሊያወግዘው ይገባል፡፡
ይህ የግብፅ የቀቢጸ ተስፋ ሙከራ ኢትዮጵያን ከልማት ጉዞዋ እንደማያስቆማት ሊታወቅ ይገባል፡፡ ኢትዮጵያ እንደሁል ጊዜው በጀግኖች ልጆቿ የተባበረ ክንድ ሉዓላዊነቷን እና ብሔራዊ ጥቅሟን ታስከብራለች፡፡
#ኢትዮጵያ #ትልቅሀገር #ትልቅሕዝብ #ታላቅርዕይ
በቤተልሔም ግርማ