Fana: At a Speed of Life!

የኢትዮጵያ ቀጣናዊ ጠንካራ ማዕከልነት ሚና

አዲስ አበባ፣ መስከረም 26፣ 2019 (ኤፍ ኤም ሲ) ኢትዮጵያ በምስራቅ አፍሪካ ሰላምና መረጋጋት እንዲሁም ለዓለም አቀፍ የንግድ መስመሮች ወሳኝ የማዕከልነት ሚና የምትጫወት ታላቅ ሀገር ናት፡፡

በተጨማሪም ኢትዮጵያ የሰው ልጅ መነሻ፣ የነጻነት ምልክት፣ የጂኦፖለቲካ ማዕከል እና የጥበብ ምድር ናት።

የኢትዮጵያውያን የአንድነት እና የቆራጥነት ውጤት የሆነው የዓድዋ ድል የፓን-አፍሪካኒዝም እንቅስቃሴ መሠረት በመሆን በአፍሪካ፣ በካሪቢያን እና በመላው ዓለም የሚገኙ የተጨቆኑ ሕዝቦችን የነጻነት መንፈስ ያነሳሳ ችቦ ሆኖ አገልግሏል።

በመሆኑም ይህንን ታላቅ ታሪካዊ ሚና በጥልቀት በመረዳት እና በመጠበቅ ለቀጣዩ ትውልድ ማስተላለፍ የሁላችንም ሀገራዊና ታሪካዊ ኃላፊነት ነው።

የአፍሪካ ቀንድ በዓለም አቀፍ የንግድ መስመርና በጂኦፖለቲካዊ አቀማመጧ ሳቢያ ሁልጊዜም የኃያላን ሀገራት የትኩረት ማዕከል ናት። በአካባቢው ቀጣናዊ መረጋጋት እና ትብብር ለማረጋገጥ አዲሱ የመደመር መንግሥት የሚጫወተው ሚና እጅግ ከፍተኛ እና ስትራቴጂካዊ ነው፡፡

ለዚህም ማሳያ የኢትዮጵያ ፕሬዚዳንት ታዬ አጽቀ ሥላሴ በቀጣናው ያሉ ኃይሎች የሕዝቦችን በሰላምና በብልጽግና የመኖር መሠረታዊ መብት እንዲያከብሩ ያቀረቡት ጥሪ ነው፡፡

ለጎረቤት ሀገራት ትብብር ቅድሚያ የሚሰጠውን የመደመር መንግሥት የዲፕሎማሲ አቅጣጫ ከቃላት ባለፈ በተግባር የኢትዮጵያ ቀጣናዊ ግንኙነት ወደ ጽኑ ስልታዊ አጋርነት እንዲሸጋገር አድርጓል፡፡

እንዲሁም የምስራቅ አፍሪካ ቀጣናን በመሰረተ ልማት ከማስተሳሰር ባለፈ በቀጣናው ሽብርተኝነትና አለመረጋጋትን በጋራ መከላከልና የሰላም አስከባሪ ኃይል የማሰማራት ስራዎችም ለቀጣናው ትስስር ተስፋ ፈንጣቂ ነው፡፡

በአሁኑ ወቅት ኢትዮጵያ ለጎረቤት ሀገራት ቅድሚያ በሚሰጠው የውጭ ፖሊሲዋ መሰረት ከቀጣናው ሀገራት ጋር የጠበቀ ግንኙነት በመፍጠር ፍሬ ማፍራት ችላለች፤ አሁንም አጠናክራ የምትቀጥል መሆኑን አረጋግጣለች፡፡

የመደመር መንግሥት የውጭ ጉዳይ ፖሊሲና ስትራቴጂ ኢትዮጵያ ከቀጣናው ሀገራት ጋር ያላትን ግንኙነት በጋራ ተጠቃሚነት ላይ መሰረት ያደረገ የፖለቲካ፣ የኢኮኖሚና የፀጥታ ትስስር ማጠናከርንም ያጠቃለለ ነው፡፡

አዲሱ የመደመር መንግሥት በቀጣናው ሰላምና ትብብር ላይ የሚኖረው ሚና እና ከጎረቤት ሀገራት ጋር የሚኖረው ግንኙነት የሀገሪቱን ብቻ ሳይሆን የመላው ቀጣና የወደፊት ዕጣ ፈንታ ለመወሰን ቁልፍ ሚና አለው።

በአጠቃላይ በዴሞክራሲያዊ፣ ሰላማዊ እና ህጋዊ መንገድ የምርጫ ሂደት የተመሰረተው የመደመር መንግሥት ኢትዮጵያ በአፍሪካ ቀንድ ሰላም፣ ልማትና መረጋጋት የምትጫወተውን ቁልፍ ሚና አጠናክራ ትቀጥላለች፡፡

#የመደመር_መንግሥት

በትዕግስት ግዛቸው

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.