የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በ1ኛ ልዩ ስብሰባው በቀረበ ረቂቅ አዋጅ ላይ እየተወያየ ነው
አዲስ አበባ፣ መስከረም 27፣ 2019 (ኤፍ ኤም ሲ) የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በፌደራል መንግሥት አስፈጻሚ አካላት ስያሜ፣ አደረጃጀት፣ ስልጣንና ተግባር ለመወሰን በቀረበው ረቂቅ አዋጅ ላይ እየመከረ ይገኛል።
ምክር ቤቱ እያካሄደ በሚገኘው 1ኛ ልዩ ስብሰባው የመንግሥት ተወካይ አቶ ፍቃዱ ተሰማ በረቂቅ አዋጁ አስፈላጊነት ላይ ማብራሪያ አቅርበዋል።
ከዚህ በፊት የነበሩት ሚኒስቴር መስሪያ ቤቶች 22 ሆነው እንደሚቀጥሉ በማብራሪያቸው ላይ አመልክተዋል።
በተጨማሪም ሁለት ሚኒስቴር መስሪያ ቤቶች ላይ የስያሜ ለውጥ መደረጉንና ሁለት ሚኒስቴሮች አንደ አዲስ መቋቋማቸው ተብራርቷል።
ቀድሞ “የባህልና ስፖርት ሚኒስቴር” የነበረው በአዲሱ “የወጣቶች እና ስፖርት ሚኒስቴር” በሚል እንዲሁም ቀድሞ “የቱሪዝም ሚኒስቴር” የነበረው በአዲሱ “የባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር” በሚል መቋቋማቸው ተጠቁሟል።
በተጨማሪም ቀድሞ “የፕላንና ልማት ሚኒስቴር” የነበረው “የብሔራዊ ስትራቴጂ ሚኒስቴር” በሚል የተቋቋመ ሲሆን፤ ቀድሞ “የትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ሚኒስቴር” የነበረው “የሎጂስቲክስ ሚኒስቴር” በሚል ስያሜያቸው መቀየሩ ተገልጿል።
በሚኒስቴር መስሪያ ቤቶቹ ላይ ማሻሻያው ያስፈለገው ይበልጥ ውጤታማ ለማድረግና ከተልዕኳቸው ጋር ለማጣጣም መሆኑም ተብራርቷል።
በረቂቅ አዋጁ ላይ የፕላንና ልማት ሚኒስትር ፍጹም አሰፋ (ዶ/ር) ማብራሪያ እያቀረቡ እንደሚገኙ ከምክር ቤቱ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡