ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ ከናይጄሪያ ፌዴራል ሪፐብሊክ ምክትል ፕሬዚዳንት ሴናተር ካሺም ሼቲማ ጋር ተወያዩ
አዲስ አበባ፣ መስከረም 27፣ 2019 (ኤፍ ኤም ሲ) ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ ከናይጄሪያ ፌዴራል ሪፐብሊክ ምክትል ፕሬዚዳንት ሴናተር ካሺም ሼቲማ ጋር ተወያይተዋል፡፡
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው ባሰፈሩት መልዕክት፤ኢትዮጵያ እና ናይጄሪያ በትብብር ሊሰሩባቸው በሚችሏቸው የሁለትዮሽ ትብብር መስኮች ዙሪያ በዛሬው ዕለት ከናይጄሪያ ፌዴራል ሪፐብሊክ ምክትል ፕሬዝዳንት ሴናተር ካሺም ሼቲማ ጋር ተወያይተናል ብለዋል።
በውይይታቸውም ኢትዮጵያና ናይጄሪያ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ በሚያደርጉት ትብብርና የልምድ ልውውጥ ላይ በስፋት መምከራቸውን ገልጸዋል።
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ናይጄሪያ በሰቆጣ ቃል ኪዳን የተገኘውን ተጨባጭ ስኬት በመገንዘብ የኢትዮጵያን ልምድ ለመቅሰም በልዑካኗ በኩል ላደረገችው ጉብኝት ምስጋናቸውን አቅርበው፤ ምክትል ፕሬዚዳንት ሴናተር ካሺም ሼቲማ በሀገራቸው የሥርዓተ ምግብን ለማሻሻል የሚያሳዩት ቁርጠኝነትም ለአህጉራችን አርአያ የሚሆን ነው ብለዋል።
ኢትዮጵያና ናይጄሪያ በስትራቴጂካዊ አጋርነት የተሣሠሩ መሆናቸውን ጠቁመው፤ የሁለቱ ሀገራት ከፍተኛ የሕዝብና የኢኮኖሚ አቅም በተቀናጀ መልኩ መሠማራት አፍሪካን በተሻለ መንገድ ለመቅረጽ ያለውን ዐቅም በይበልጥ ያጎላል ነው ያሉት።
ኢትዮጵያ ለናይጄሪያ የዲፕሎማቲክና የሰርቪስ ፓስፖርት አሠራሮችን ማሻሻሏን እንዲሁም የዲፕሎማቲክና የሰርቪስ ፓስፖርት ለያዙ የናይጄሪያ ዜጎች የቪዛ ነጻ የጉዞ ሥርዓትን በሥራ ላይ ማዋሏን አመልክተዋል፡፡
ይህም በሁለቱ ሀገራት መካከል ያለውን የሰዎች ለሰዎች ግንኙነትና የዲፕሎማሲያዊ ትሥሥር የበለጠ ለማጠናከር የሚያስችል ዐቅም ነው ብለዋል።
በኢንቨስትመንት ዘርፍም አሊኮ ዳንጎቴ በኢትዮጵያ ልማት ውስጥ እያበረከቱ ያሉትን ጉልህ አስተዋጽኦ አንስተው፤ በተጨማሪም ሌሎች የናይጄሪያ ባለሀብቶች በኢትዮጵያ በተለያዩ ዘርፎች ኢንቨስት ሊያደርጉ ስለሚችሉባቸው ዕድሎች መወያየታቸውን አስረድተዋል፡፡