Fana: At a Speed of Life!

የእንቆቅልሹ መልስ

የዘመናት እንቆቅልሽ! ትልቅ ሀገር ትንሽ ኢኮኖሚ። ትልቅ ሕዝብ፤ ነገር ግን በድህነትና በኋላቀርነት የሚኖር። ትልቅ፤ ነገር ግን ርዕይ አልባ ሆና የቀየች ሀገር፤ ኢትዮጵያ! ለዘመናት ሳይፈታ የቆየ እንቆቅልሽ!

ኢትዮጵያ በታሪኳ ረጅም ዘመን ያስቆጠረች፣ የራሷ ፊደል፣ የቀን አቆጣጠር እና የጥንታዊ ሥልጣኔ ባለቤት የሆነች ትልቅ ሀገር ናት።

ሆኖም ይህ የሀገራችን ተፈጥሮአዊ ሀብት፤ ታላቅ ታሪካዊና ባህላዊ ቅርስ በሳይንስ፣ በቴክኖሎጂ እና በጠንካራ የኢኮኖሚ መዋቅር ሳይደገፍ ዘመን ሄዶ ዘመን እስኪተካ እዚህ ትውልድ ላይ ደረሰ።

ታዋቂው የፖለቲካ ሳይንቲስት፣ የጂኦፖለቲካ ተመራማሪና የኢኮኖሚክስ ባለሙያ ፍራንሲስ ፉኩያማ “Trust: The Social Virtues and the Creation of Prosperity” በተሰኘው መጽሐፉ፥ “ሀብት ብቻውን ብልጽግናን አያረጋግጥም!” ይላል። እንዳውም፣ ጠንካራ ተቋማትና ስትራቴጂካዊ አመራር የሌላቸው ሀገራት የተፈጥሮ ጸጋቸው ወደ ሀብት ሳይሆን ወደ ቀውስ ሊቀየር እንደሚችልም ያስረዳል።

ኢትዮጵያ የናይል ወንዝ መነሻ፣ ለም መሬት እና እጅግ ሰፊ የተፈጥሮ ሀብት ያላት ምድር ሆና ሳለ፣ በሚሊየኖች የሚቆጠሩ ዜጎቿ በድህነትና ኋላቀርነት ሲማቅቁ፤ ሀገራቸውም የ’’ረሃብ ምሳሌ’’ ተደርጋ ስትጠራ “ዘመን ባልፈታው የድህነት አዙሪት ውስጥ ኖራለች። የዚህ ታሪካዊ ማነቆ ቁልፍ መነሻ የሀብት ማጣት ሳይሆን፣ ትውልድ ተሻጋሪ ታላቅ ርዕይ እና የስትራቴጂያዊ አመራር ማጣት ነበር።

የእንቆቅልሹ ፍቺ

የኢትዮጵያ የህላዌ እንቆቅልሽ፤ እልህ እና ቁጭት የፈጠረበት የመደመር መንግሥት እንቆቅልሹን ለመፍታት እየታተረ ነው፡፡ ኢትዮጵያ አሁን ላይ የጀመረቻቸው ተስፋ ፈንጣቂ ሥራዎች ብቃት ያለው መሪነትና ርዕይ ሲኖር የተፈጥሮ ጸጋን እንዴት ወደ ላቀ ሀብት መለወጥ እንደሚቻል በተግባር እያሳዩ ነው።

አሁን በኢትዮጵያ እየፈኩ ያሉት እመርታዊ ለውጦች በዋናነት የመደመር የአመራር ጥበብ ውጤቶች ናቸው።

በተግባር የተከናወኑት የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ መጠናቀቅ፤ ለረጅም ዓመታት ተተብትቦ የነበረውን የሀገሪቱን የኢኮኖሚ መዋቅር ወደ ላቀ ምዕራፍ ያሸጋገረውና ያዘመነው የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ ርምጃ፤ ሀገራዊ የምግብ ዋስትናን ያረጋገጠው የበጋ ስንዴ ልማት እና የከተሞቻችንን ኢኮኖሚያዊ ንቅናቄ ያፋጠኑት የኮሪደር ልማት ፕሮጀክቶች የመደመር ሥልጣኔ ፍሬዎች ናቸው።

አዲሱ የታሪክ እጥፋት – ሁለንተናዊ ዝግጅት

የረጅም ዘመን የሥነ መንግሥት ታሪክ እና የሥልጣኔ ባለቤት የሆነች ሀገር በቂ ዝግጅት ባለማድረጓ ብዙ ርቀት የወሰዳት የቁልቁለት ጉዞ ተጓዘች። የውስጥ ሽኩቻ እና የእርስ በርስ ጦርነት ልማዷ እንዲሆን ተደርጋ ቆየች። በተደጋጋሚ ለድርቅና ረሃብ ተጋልጣ ኖረች።

ከተፈጥሮአዊ የባሕር በር መግቢያና መውጫ ባቤትነቷ ተገፍታ ወደብ አልባ ሀገር ተደረገች። ይህ እንዴት ይሆናል? ሲል የመደመር መንግሥት በቁጭትና በድፍረት ጠየቀ።

ዘመናትን የተሻገረው የድህነትና የኋለቀርነት መገለጫችን እንቆቅልሽ በተግባራዊ የመሪነት ብቃትና በታላቅ ርዕይ እየተፈታ ይገኛል።

የመደመር መንግሥት የረዥም ጊዜ ትልም ከውጭ ርዕዮተ ዓለሞች ጥገኝነት የፀዳ፣ በሀገር በቀል እውቀትና እሴቶች ላይ የተመሰረተ የመደመር ሥልጣኔን በመተግበር ላይ የተመሠረተ ነው።

የመደመር ሥልጣኔን እውን የምናደርገው የታሪክ ስብራቶቻችንን ከመጠግን እና ጉድለቶቻችንን ከመሙላት አልፈን፤ ሀገራችን ለማንኛውም ከባቢያዊ እና ዓለም አቀፋዊ ፈተና የማይበገር ሁለንተናዊ ዝግጅት እንድታደርግ በሚያስችል መንገድ መሆኑንም የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የፓርላማ ንግግር ያስገነዝበናል።

በግፍ የተወሰደብንን የባህር በር … በመደመር…

ሀገራችን ለአሁኖቹም ሆነ ለመጪዎቹ ዓለም አቀፋዊና አህጉራዊ ፈተናዎች ራሷን በተሟላ ሁኔታ እንድታዘጋጅ እያደረጋት ያለው በመደመር የሥልጣኔ መንገድ ነው።

ይህ የኢትዮጵያ ሥልጣኔ ምሉዕ የሚሆነው ኢትዮጵያ በውስጥና በውጭ ኃይሎች ሴራ በግፍ የተወሰደባትን የባህር በር ባለቤትነት በዘመናዊ የአመራር ጥበብ ማስመለስ ስትችል ነው።

በአጠቃላይ የመደመር ስትራቴጂ በዓለም አቀፍ መድረክ ላይ አዎንታዊና ወሳኝ ሚና የምትጫወት ሀገር ለመገንባት የሚያስችል፤ በኢትዮጵያ ዘመናዊ ታሪክ ውስጥ ትልቅ የታሪክ እጥፋት የሚመዘገብበት የሁለንተናዊ ብልጽግና ጉዞን የሚያረጋግጥ አዲስ ወርቃማ ምእራፍ ይሆናል።

#ኢትዮጵያ #ትልቅሀገር #ትልቅሕዝብ #ታላቅርዕይ

በአሰፋ አሕመድ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.