Fana: At a Speed of Life!

የመደመር መንግሥት ዘላቂ የኢነርጂ ሥርዓት ለመገንባት ቁርጠኛ ነው

አዲስ አበባ፡ ጥቅምት 5 ቀን 2019 (ኤፍ ኤም ሲ) የመደመር መንግሥት ተደራሽ፣ አስተማማኝ፣ ተመጣጣኝ እና ዘላቂ የኢነርጂ ሥርዓት ለመገንባት ቁርጠኛ መሆኑን የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር ገለጸ።
ሁለተኛው የኢትዮጵያ ታዳሽ ኢነርጂ ጉባኤ “የኢትዮጵያን የታዳሽ ኢነርጂ ሽግግር በኢንቨስትመንት፣ በፈጠራና በትብብር ማፋጠን” በሚል መሪ ቃል በአዲስ አበባ ዓለም አቀፍ ኮንቬንሽን ማዕከል እየተካሄደ ነው።
ለሶስት ቀናት በሚቆየውን በዚህ ጉባኤ ላይ የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር የኤሌክትሪፊኬሽንና የኢነርጂ መረጃ መሪ ሥራ አስፈጻሚ አቶ መስፍን ዳቢ ባደረጉት ንግግር፤ ኢትዮጵያ ያስቀመጠችውን የኤሌክትሪክ ተደራሽነት ግብ ለማሳካት ጠንካራ ትብብር፣ ቀጣይነት ያለው ኢንቨስትመንትና የጎላ የግሉ ዘርፍ ተሳትፎ ወሳኝ ነው ብለዋል።
ኤሌክትሪክ ለኢኮኖሚ ሽግግር፣ ለኢንዱስትሪ ዕድገት፣ ለግብርና ምርታማነትና ለህዝብ አገልግሎት መሻሻል መሠረታዊ ሚና እንዳለው ጠቅሰው፤ ኤሌክትሪክ በተመጣጣኝ ዋጋ ለሁሉም ማዳረስ ለአገሪቱ አጠቃላይ የልማት ግቦች ስኬት ቁልፍ መሆኑን አስገንዝበዋል።
በተለይም ከብሔራዊ የኤሌክትሪክ መረብ ርቀው ለሚገኙ ማህበረሰቦችና የንግድ ተቋማት ዘላቂ የኃይል አቅርቦትን ለማረጋገጥ የቤት ውስጥ የሶላር ኃይል አቅርቦት ሥርዓቶች፣ አነስተኛ የሶላር ኤሌክትሪክ መረቦች እና ምርታማነትን የሚያሳድጉ የኢነርጂ ቴክኖሎጂዎችን ተደራሽ ማድረግ ጉልህ ድርሻ እንዳላቸው ጠቁመዋል።
ኢትዮጵያ ያላትን ሰፊ የታዳሽ ኢነርጂ ሀብት በአግባቡ መጠቀም የኢነርጂ ደኅንነትን እንደሚያጠናክር ገልጸዋል።
በተጨማሪም ዘላቂ የኢኮኖሚ ዕድገትን ለማስመዝገብና የኢነርጂ ሥርዓቱን የመቋቋም አቅም ለማሳደግ ትልቅ ዕድል እንደሚፈጥር አቶ መስፍን ተናግረዋል።
የግሉ ዘርፍ ለኢነርጂ ልማት የሚያመጣው ካፒታል፣ ቴክኒካዊ እውቀት፣ ፈጠራና የስርጭት አቅም የታዳሽ ኢነርጂ መፍትሔዎችን በስፋት ለማዳረስ፣ የሥራ ዕድሎችን ለመፍጠርና የአገር ውስጥ የማምረት አቅምን ለማጠናከር ወሳኝ መሆኑን አስገንዝበዋል።
ይህንን ለማሳካት ግልጽ የፖሊሲ ማዕቀፍና ተገቢ የቁጥጥር ሥርዓት፣ የፋይናንስና የውጭ ምንዛሬ ተደራሽነት፣ እንዲሁም በሚመለከታቸው ተቋማት መካከል ውጤታማ ቅንጅት መፈጠር እንዳለበት ጠቁመዋል።
የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር ከተለያዩ ተቋማት፣ ከግሉ ዘርፍ እና ከልማት አጋሮች ጋር በትብብር በመሥራት ለኢትዮጵያ ተደራሽ፣ አስተማማኝ፣ ተመጣጣኝና ዘላቂ የኢነርጂ ሥርዓት ለመገንባት ቁርጠኛ መሆኑን አረጋግጠዋል።
መሪ ሥራ አስፈጻሚው አበክረው እንደገለጹት፣ ጉባኤው በህብረተሰቡ የኑሮ መሻሻልና በኢኮኖሚው ላይ በሚያመጣው ተጨባጭ ለውጥ የሚለካ ነው።
ጉባኤው የኢንቨስትመንት እንቅስቃሴዎችን ማጠናከር፣ አዳዲስ የፋይናንስ አማራጮች፣ በግብርናና በሌሎች ምርታማ ዘርፎች የታዳሽ ኢነርጂ አጠቃቀም፣ እንዲሁም የአገር ውስጥ ማምረቻና የንጹሕ ኢነርጂ ገበያን ማጠናከር በሚመለከቱ ጉዳዮች ላይ ሰፊ ውይይትና የልምድ ልውውጥ ያደረጋል ተብሎ ይጠበቃል።
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.