Fana: At a Speed of Life!

ደንበኞች የቆጣሪ ንባባቸውን በቴሌግራም ቻትቦት የሚያሳውቁበት አዲስ አሰራር ወደ ሥራ ገባ

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 6፣ 2019 (ኤፍ ኤም ሲ) የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት የድህረ ክፍያ ተጠቃሚ የመኖሪያ ቤት ደንበኞች ወርሃዊ የቆጣሪ ንባባቸውን በራሳቸው ማሳወቅ የሚያስችላቸውን የቴሌግራም ቻትቦት አበልጽጎ ወደ ሥራ አስገብቷል።

አዲሱ አሰራር በመደበኛው የቆጣሪ ንባብ ወቅት ንባባቸው ያልተወሰደላቸው ደንበኞች ትክክለኛውን የቆጣሪ ንባብ በተፈቀደው የጊዜ ገደብ ማለትም ከመደበኛው የንባብ ወቅት ማብቂያ በኋላ ባሉት 4 ተከታታይ ቀናት ውስጥ በቀጥታ እንዲያስገቡ ያስችላል።

አገልግሎቱ በመላ ሀገሪቱ ለሚገኙ ነጠላ ፌዝ ቆጣሪ ያላቸው የድህረ ክፍያ ተጠቃሚ የመኖሪያ ቤት ደንበኞች ብቻ የተዘጋጀ መሆኑን አገልግሎቱ ለፋና ዲጂታል የላከው መረጃ ያመላክታል፡፡

በመሆኑም ደንበኞች በቴሌግራም ላይ ‘@Eeuchatbot’ ብለው በመፈለግ ወይም በተቋሙ ይፋዊ የማኅበራዊ ሚዲያ ገጾች ላይ የቻትቦቱን ማስፈንጠሪያ በመጠቀም አገልግሎቱን ማግኘት ይችላሉ።

ደንበኞች ቻትቦቱን ካስጀመሩ በኋላ “Send Meter Reading” የሚለውን አማራጭ በመምረጥ ባለ 12 ዲጂት የደንበኛ መለያ ቁጥር (Contract Account Number) በማስገባት ትክክለኛውን የቆጣሪ ንባብ በማስገባት መላክ እንደሚችልም አመልክቷል፡፡

ደንበኞች ንባባቸውን ማስገባት የሚችሉት በተፈቀደው የጊዜ ገደብ ውስጥ ብቻ እንደሆነ እና ከተፈቀደው ጊዜ በፊት ወይም ከገደቡ በኋላ ንባብ እንዲሁም የተሳሳተ ንባብ ማስገባት የማይቻል መሆኑንም አሳስቧል።

ይህ አዲስ አሰራር በቆጣሪ ንባብ አለመወሰድ ምክንያት ሊፈጠሩ የሚችሉ የፍጆታ ሒሳብ አዘገጃጀት ችግሮችንና የክፍያ መዘግየት ቅሬታዎችን ለመቀነስ የታለመ ሲሆን፣ ደንበኞች በቀላሉና በተመቻቸ መንገድ የቆጣሪ ንባባቸውን እንዲያሳውቁ ዕድል እንደሚፈጥርም ነው የተገለጸው።

#ኢትዮጵያ #ትልቅሀገር #ትልቅሕዝብ #ታላቅርዕይ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.