የትውልዱ ኃላፊነት፡ የኢትዮጵያን ሁለንተናዊ ብሔራዊ ጥቅም ማስጠበቅ
አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 7፣ 2019 (ኤፍ ኤም ሲ) ብሔራዊ ጥቅም ለአንድ ሀገር የህልውና መሰረት ነው፤ ኢትዮጵያ ብሔራዊ ጥቅሟ ከታሪክ፣ ከጂኦፖለቲካ፣ ከኢኮኖሚ እንዲሁም ከዜጎች የወደፊት ተስፋ አንጻር ይቃኛል፡፡
ብሔራዊ ጥቅም ማስከበር ማለት ለግለሰቦች፣ ለመሪዎች እንዲሁም ለተቋማት የሚደረግ ሳይሆን፤ ለሀገር ህልውናና ሉዓላዊነት መከበር የሚገባውን ዋጋ መክፈል ነው፡፡
የነጻነት ተምሳሌት ለሆነችው ኢትዮጵያ፤ ነጻነትና ሉዓላዊነቷን ማስጠበቅ ለድርድር የማይቀርብ ብሔራዊ ጥቅሟ ነው፡፡
ኢኮኖሚያዊ አቅምን ማሻሻል፣ ለወጣቶች የስራ እድል መፍጠር፣ የምግብ ሉዓላዊነትን ማስጠበቅ፣ የተገባን አኗኗር ለዜጎቿ መስጠት ደግሞ ሌላኛው የማትደራደርበት ብሔራዊ ጥቅሟ ነው፡፡
እንዲሁም የተፈጥሮ ሀብቶቿን ፍትሀዊና የጋራ ተጠቃሚነትን መሰረት ባደረገ መንገድ በማልማት መሠረታዊ ብሔራዊ ጥቅሟን ለማስጠበቅ ትሰራለች፡፡ ይህም የጎረቤት ሀገራትን በኃይል ለማስተሳሰርና በጋራ ለማደግ ወሳኝ አካሄድ ነው፡፡
ኢትዮጵያ ይህን ለማስጠበቅ ደግሞ ሁለቱ የውሃ ሀብቶቿን በአግባቡ ለመጠቀም ትሰራለች፤ ታላቁን የህዳሴ ግድብ በህዝቦቿ ደምና ላብ ያለማንም የውጪ እርዳታ ገድባ ከራሷ አልፋ ለቀጣናው ሀገራት የኃይል አቅርቦቷን አሳድጋለች፡፡
ታሪክም ህግም የሚመሰክሩለትን የባሕር በር ባለቤትነቷንም ዲፕሎማሲያዊ በሆነ መንገድ ጥያቄዋን አንስታ እየሰራች ከተለያዩ ሀገራትም ድጋፎችን እያገኘች ትገኛለች፡፡
ወቅቶች ይቀያየራሉ፣ ሰዎች በጊዜያቸው ኖረው ያልፋሉ፣ ሀገር ግን ትናንቷን በኩራት የምናነሳላት፣ የምንመካባት፣ ለነገም የምናቆያት የማንለውጣት፣ ጠይቀን ያገኘናት ሳይሆን፤ በስጦታነት የተቀበልናት ቅርሳችን ናት፡፡
ጥያቄው የሚሆነው ለትውልድ ምን አይነት ሀገር እናቆያለን የሚለው ነው፡፡
ሀገር የትውልድ አደራ ናት፤ አባቶች ደምና አጥንታቸውን ከስክሰው፣ ከነጻነትና ክብሯ ጋር ያስረከቧት፣ ልጆችም ተቀብለው ሉዓላዊነትና ብሔራዊ ጥቅሟን አስጠብቀው ለልጆቻቸው የሚያቆይዋት ናት፡፡
ኢትዮጵያ ዜጎቿን ትወክላለች፣ ዜጎቿም እርሷን ይወክላሉ፣ ሀገርን መወከል ታድያ በሚያስፈልጋት ነገር ሁሉ ከፊት ቀድሞ መገኘት እንደሆነ ይታመናል፡፡
በሀገር ላይ የሚነሱ ብሔራዊ ጥቅምን አደጋ ላይ የሚጥሉ የእኛነት ስሜትን የሚያደፈርሱ የውስጥ አለመግባባቶችን በውይይት መፍታትና በጋራ መቆም፤ ለውጪ ጠላቶች ሽንቁሮችን አለመተው ደግሞ ከዜጎች የሚጠበቅ ይሆናል፡፡
በቤተልሔም ግርማ