Fana: At a Speed of Life!

በሞባይል ባንኪንግ ማጭበርበር ወንጀል የተጠረጠሩ 37 ግለሰቦች በቁጥጥር ሥር ዋሉ

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 7፣ 2019 (ኤፍ ኤም ሲ) የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ከሌሎች የጸጥታና ፍትህ አካላት ጋር በመቀናጀት ባካሄደው ኦፕሬሽን በሞባይል ባንኪንግ ማጭበርበር ወንጀል በ658 ዜጎች ላይ ከ200 ሚሊየን ብር በላይ ጉዳት ያደረሱ 37 ተጠርጣሪዎችን በቁጥጥር ሥር አውሎ ምርመራ እያጣራባቸው መሆኑን ገልጿል።
ተጠርጣሪዎቹ በቡድን በመደራጀት የባንክ የቴክኒክ ድጋፍ ሰጪ ሠራተኛ በመምሰል “ሽልማት ደርሶዎታል”፣ “ሞባይል ባንኪንግ ሲስተም ልናዘምንልዎት ነው” እንዲሁም “የባንክ ሂሳብዎን ከፋይዳ መታወቂያዎ ጋር ለማስተሳሰር ነው” በሚል ስልክ በመደወል የይለፍ ቃል፣ OTP፣ PIN ወይም ሌሎች ሚስጥራዊ መረጃዎችን በመጠየቅ እና የተለያዩ ማጭበርበሪያ ዘዴዎችን በመጠቀም ሲያጭበረብሩ እንደነበር ፖሊስ በምርመራው አረጋግጧል።
ተጠርጣሪዎቹ በቡድን ተደራጅተው መኖሪያ ቤት በመከራየት፣ በተለያዩ ሰዎች ስም የወጣ በርካታ የባንክ አካውንትና ሲም ካርዶችን ከግለሰቦች ላይ በመግዛት እና በመከራየት የወንጀል ተግባሩን ይፈፅሙ እንደነበር ፖሊስ በምርመራ ደርሶበታል።
ተጠርጣሪዎቹ ለወንጀል ተግባሩ ይገለገሉበት ከነበረው ከዘጠኝ ተሽከርካሪዎች፣ ከአንድ ሞተር ሳይክል፣ ከ114 ሞባይል ቀፎዎች እና ከ478 ሲም ካርዶች ጋር በቁጥጥር ሥር ማዋሉን ፖሊስ አስታውቋል።
የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ የሞባይል ባንኪንግ ማጭበርበር ወንጀልን ለመከላከል የጀመረውን ኦፕሬሽን አጠናክሮ መቀጠሉን ገልጾ፤ በአጭበርባሪዎቹ ጉዳት የደረሰበት ማንኛውም ሰው በዜጎች ተሳትፎ መተግበሪያ (EFPApp)፣ በነፃ የስልክ መስመር (991)፣ በሰው አልባ ስማርት ፖሊስ ጣቢያ (SPS) እንዲሁም በኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ወንጀል ምርመራ ጠቅላይ መምሪያ ቢሮ በአካል በመቅረብ ጥቆማ መስጠት እንደሚችል ጥሪ አቅርቧል።
በተጨማሪም ባንኮች በግል ስልክ በመደወል ምንም ዓይነት አገልግሎት እንደማይሰጡ ሕብረተሰቡ ተገንዝቦ አጠራጣሪ የስልክ ጥሪዎች ሲያጋጥሙ የቀረቡለትን ጥያቄዎች አምኖና ተቀብሎ እርምጃ ከመውሰዱ በፊት ጉዳዩን ወዲያውኑ ለፖሊስ ወይም ለባንክ ማሳወቅ እንዳለበት ፖሊስ አሳስቧል።
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.