የኢትዮጵያ ስልጣኔ እውን የሚሆንበትን መንገድ የመሥራት ኃላፊነት አለብን – ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር)
አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 11፣ 2019 (ኤፍ ኤም ሲ) የኢትዮጵያ ስልጣኔ እውን የሚሆንበትን መንገድ የመሥራት ኃላፊነት አለብን አሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ የኢትዮጵያ የኒውክሌር ሀይል ኮሚሽንን በጎበኙበት ወቅት÷ በልቶ ማደር ብቻ ሳይሆን ለልጆቻችን በሁሉም መስክ ወረት ማስቀመጥ ያስፈልጋል ብለዋል፡፡
ኢትዮጵያውያን ያገኙትን ሁሉ በአንድ ጊዜ ተጠቅመው የሚጨርሱ አይደሉም ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለክፉ ቀን ብለው ይቆጥባሉ ይህን ባህል በዚህ ዘመን መተግበር እንደሚገባ ጠቁመዋል።
በተሰጠን ጊዜ፣ በተሰጠን እድል ለልጆቻችን ጥሪት፣ ሀብት እና መሰረት ማስቀመጥ እንደሚገባ በማንሳት ለነገ የሚተርፍ ሥራን ለመስራት እና ከትውልድ ትውልድ ለማስተላለፍ በትውልድ ቅብብሎሽ የሚሰራ ሥራ እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል።
ስፔስ ሳይንስ እና ኒውክሌር ላይ ዘግይተናል ነገር ግን የተጀመሩ ሥራዎች ተጠናክረው በምግብ ራሷን የምትችል ከዛም አልፎ የምትሸጥ፣ ጤናን በመጠበቅ ረገድ በቂ አቅም ያላት፣ በጤና ቱሪዝም ከፍተኛ ሀብት የምታስገባ፣ ኢነርጂ የምታመርትና የምትሸጥ ባላት የኢነርጂ አቅርቦት በርካታ ኢንቨስትመንቶችን የምትስብ ከነዚህ ትሩፋቶች ደግሞ መሰረተ ልማቶችን መገንባት የምትችል ሀገርን መስራት የሁላችንም ኃላፊነት ነው ብለዋል፡፡
ዘላቂ ተቋማትን መገንባት የምትችል የሥራ ባህሏን ከዘመኑ ስልጣኔ ጋር አጣጥማ የምትይዝ ሀገር፣ ከሕግ ባሻገር ሞራል የሚገዛው፣ ሌብነትን የሚጠየፍ እና መሥራት ክብር እንደሆነ የሚያምን ትውልድ እንደሚፈጠር ያላቸውን እምነት ገልፀዋል፡፡
ኢትዮጵያ በምናስባት ልክ እና ቦታ ሆና ማየት የምንችለው ኃላፊነት ተሰምቶን ለረጅም ጊዜ አስበን እና አቅደን መሥራት እና የምንሰራውን ሥራ ልጆቻችን የሚረከቡበትን አካሄድ ስንከተል ብቻ ነው ብለዋል።
በሚቀጥሉት 25 ዓመታት ኢትዮጵያ በሁሉም መስክ አስተማማኝ መሰረት ጥላ በአፍሪካ ምሳሌ እና ግንባር ቀደም አርዓያ እንደምትሆንም ጠቁመዋል።
በእመቤት ሲሳይ