Fana: At a Speed of Life!

የኤርትራ ሕዝብ ‘ከነጻነት በኋላ’ የነበረውን ሁሉ አጥቷል – ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር)

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 9፣ 2019 (ኤፍ ኤም ሲ) የኤርትራ ሕዝብ ‘ከነጻነት በኋላ’ ኤርትራ የኢትዮጵያ አካል በነበረችበት ጊዜ የነበረውን ሁሉ አጥቷል አሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በትግርኛ ቋንቋ ባደረጉት ቆይታ እንዳሉት፤ ኤርትራ የኢትዮጵያ አካል በነበረችበት ወቅት ያበቡና ያሸበረቁ የነበሩት ከተሞቿ አሁን ላይ የመንደር ያህል ሆነዋል፡፡

በወቅቱ ኤርትራ ከ300 በላይ ኢንዱስትሪዎች እንደነበሯትና በአፍሪካ በኢንዱስትሪ በለጸጉ ከሚባሉት አንዷ እንደነበረች አስታውሰው፤ ዛሬ ግን አስመራን ለአብነት ብትወስድ ከአርባ ምንጭ እና ጅግጅጋ የምታንስ ከተማ ሆናለች ብለዋል፡፡

ምጽዋ ባዶ ሆናለች፤ አሰብ ሰው አልባ ከተማ ሆናለች ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ የኤርትራ ሕዝብ ‘ከነጻነት በኋላ’ የነበረውን ሁሉ ማጣቱን ገልጸዋል፡፡

የኤርትራ አገዛዝ ልማትና ተቋማትን መገንባቱን ትቶ የኢትዮጵያ ጠላቶች መሳሪያ በመሆኑ፤ ሥራ ወዳድና እንግዳ ተቀባይ የነበረው የኤርትራ ሕዝብ ዛሬ ስደትና እንግልት መገለጫው ሆኗል ነው ያሉት፡፡

እንደዚህ አይነት ድርጊቶች ጉርብትናን የሚያበላሹ መሆናቸውን ገልጸው፤ አይዞህ ባዮችም ቢሆኑ ጥይት ከማቀበል በዘለለ የኤርትራን ችግር ሊፈቱ አይችሉም ብለዋል፡፡

ምክንያቱም እነዚህ አካላት የኤርትራ ችግር መፈታት የማይገዳቸውና የራሳቸውን ችግር መፍታት ያልቻሉ መሆናቸውን አስረድተዋል፡፡

የሚያዋጣው ጥሩ ጉርብትናና ወዳጅነት ብቻ መሆኑን የገለጹት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ባለፉት 35 ዓመታት እንደታየው ከዚህ ውጭ ያለው መንገድ እንደማያዋጣ አጽንኦት ሰጥተዋል፡፡

 

የልማት አጋር መሆን እየተቻለ የጠላቶች መጫወቻ መሆን አያዋጣም በሚል ያቀረብናቸውን ጥሪዎች ጆሮ ዳባ ማለት አደጋው እጅግ ከባድ ይሆናል ሲሉ አስገንዝበዋል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.