Fana: At a Speed of Life!

ከህገወጡ የህወሓት ቡድን በመላቀቅ ፊቱን ለልማት ያቀናው የትግራይ ህዝብ

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 11፣ 2019 (ኤፍ ኤም ሲ) የትግራይ ህዝብ ለብዙ ዘመናት ሲጎሳቆል ይበጁኛል ባላቸው ሲጎዳና ሲካድ የቆየ ህዝብ ነው፡፡ ህዝቡ ለልማት ያለውን ጉጉትና ቁርጠኝነት ያህል ከስሩ በወጡትና ነጻ እናውጣህ ባሉት በኩል ግን የታደለ አልነበረም፡፡
ህገወጡ የህወሓት ቡድን ለዘመናት በትግራይ ህዝብ ስም እየነገደ ክልሉን ወደ አዘቅት ይዞት ሲጓዝ የቆየ ቡድን ነው፡፡
ላለፉት በርካታ ዓመታት ህገወጡ ህወሓት ራሱን እንደ ትግራይ ህዝብ ወኪል ሲቆጥር ቢቆይም፤ የትግራይ ህዝብ ከጎኑ እንደማይቆም በተረዳ ወቅትም ወጣቶችን ለግዳጅ ጦርነትና አፈሳ ሲዳርግ ቆይቷል፡
ህገወጡ ህወሓት በጦር መሳሪያ ወደ ስልጣን በመምጣቱና በሰላማዊ መንገድ አብሮ የመስራት መርህን የሚገነዘብ ባለመሆኑ፤ ከጠብመንጃና ከጦርነት አዙሪት ውስጥ ከመውጣት ይልቅ ከግጭት የማትረፍ ስሌትን ተያይዟል፡፡
የትግራይ ህዝብ የተለያዩ ሰልፎችን በመውጣት ለህገወጡ ቡድን ያለውን ተቃውሞ ሲያሳይ ሌሎችም ድምፅ እንዲሆኑት ሲጠይቅ ከርሟል፡፡
ዛሬም የፌደራል መንግሥት የትግራይ ህዝብ የሚገባውን ልማት እንዲያገኝ፣ ለዳግም ግንባታና ለሰላም ያለውን ቁርጠኝነት እያየ ይገኛል፡፡
ትናንት በትግራይ ህዝብ ላይ ያደረሰው በደል ያልበቃው ይህ ህገወጡ የህወሓት ቡድን በህዝብ ገንዘብ የተሰሩ የክልሉን መሰረተ ልማቶች በማውደም፣ ጦርነትና ረሀብ ያጎሳቆላቸውን ተፈናቃዮች በማስያዣነት በመጠቀም እርዳታ ለማግኘት ያንንም ለጦር መሳሪያ ግዢ ለማዋል ይሰራ ነበር፡፡
የትግራይ ህዝብ ሰላም እንዲሰፍን፣ ከሌሎች ክልሎች እኩል ልማትና እድገት በክልሉ እንዲስፋፋ ይሻል፡፡
የትግራይ ህዝብ ለዘመናት ከሌሎች ወንድሞቹ ጋር በጋራና በመተሳሳብ የዘለቀ፣ ለሀገሩ መስዋዕትነትን የከፈለ ህዝብ ነው፤ ነገር ግን ህገወጡ ሕወሓት የትግራይን ህዝብ ከሌሎች ኢትዮጵያን ወንድሞቹ ሊነጥለው የስልጣን ማስጠበቂያ መሳሪያው ሊያደርገው በመሻት እኩይ ተግባራትን ሲፈፅም ቆይቷል፡፡
እንደ ህገወጡ ሕወሓት ያሉ ቡድኖች ግባቸው ስልጣን ብቻ በመሆኑ እኔ ከሞትኩ ሰርዶ አይብቀል አይነት አካሄድን በመከተል፣ ለትግራይ ህዝብም ሆነ ለኢትዮጵያ ቅንጣት ሳይገዳቸው ሀገር የማጥፋት ተግባርን ዓላማቸው ያደርጋሉ፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ህወሓት በትግራይ ተተኪ ትውልድ እንዳይኖር ብዙ ጥሯል፣ ከእርሱም በኋላ ትግራይ እንዳትኖር ብዙ ሰርቷል፡፡ እኔ ከሞትኩ ትግራይ የለችም እያለ እንደዚያም ሆኖ ግን አልተሳካለትም ብለዋል፡፡
በመሆኑም ህገወጥ ቡድኑ እድሜውን ለማራዘም የትግራይን ህዝብ መጠቀሚያ ለማድረግ ቢሞክርም የህዝቡ እውነተኛ ፍላጎት ግን ልማት፣ ሰላም፣ እኩልነት እንዲሁም በጋራ የመኖር ጽኑ ፍላጎት ነው፡፡
በቤተልሔም ግርማ
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.