የሽግግር ፍትሕ የሕግ የበላይነትን ለማጠናከር ወሳኝ ነው- ወ/ሮ ሐና አርዓያስላሴ
አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 13፣ 2019 (ኤፍ ኤም ሲ) የፍትሕ ሚኒስቴር እና የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች የሽግግር ፍትሕ የጋራ ፎረም ምስረታ መርሐ ግብር እየተካሄደ ነው፡፡
የፍትሕ ሚኒስትር ሐና አርዓያስላሴ በዚህ ወቅት÷ የሽግግር ፍትሕ ፖሊሲውን ለማዘጋጀት ከረዥም ጊዜ ጀምሮ የጥናትና የምክክር ሥራዎች ሲከናወኑ መቆየታቸውን አስታውሰዋል።
በዚህም በክልሎችና ከተማ አስተዳደሮች በርካታ መድረኮች መካሄዳቸውንና ከተለያዩ የማኅበረሰብ ክፍሎች ሐሳቦች መሰብሰባቸውን ተናግረዋል፡፡
ፖሊሲው በመንግሥት ምክር ቤት ከጸደቀ በኋላ ለተግባራዊነቱ የሚያስፈልጉ ሕጋዊ ማዕቀፎችን የማዘጋጀት ሥራ መከናወኑን ጠቁመዋል።
የሽግግር ፍትሕ ሒደትም በግጭቶች ምክንያት የተፈጠሩ ቁርሾዎችን ለመፍታት፣ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች ዳግም እንዳይፈጸሙ ለመከላከልና ዘላቂ ሰላምን ለማረጋገጥ ወሳኝ ነው ብለዋል።
የሽግግር ፍትሕ ሂደቱም የግጭቶችን መነሻ ምክንያቶች ለይቶ ለመፍታት፣ በማኅበረሰቡ ውስጥ የተከማቹ ቁርሾዎችን ለማስወገድና ግጭቶች በድጋሚ እንዳይከሰቱ ለመከላከል አስፈላጊ መሆኑን ገልጸዋል።
ከሀገራዊ ምክክር ሒደት ጋር የሽግግር ፍትሕ ሥራዎችን በማቀናጀት የሀገሪቱን የሰላም ግንባታ ጥረት ማጠናከር እንደሚገባ ነው ያመላከቱት፡፡
በቀጣይም የሕግ ማዕቀፎቹን በሕዝብ ተሳትፎ አጠናቆ የማጽደቅና በፖሊሲውና በሕጎቹ የተመለከቱ ተቋማትን በማቋቋም ወደ ተግባራዊ አፈጻጸም እንደሚገባ አብራርተዋል።
በዚህ ሂደት የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ሚና ወሳኝ መሆኑን ጠቁመው÷በተለይም የመብት ጥሰት ሰለባዎች፣ ሴቶችና ተጋላጭ የማኅበረሰብ ክፍሎች በሒደቱ ውስጥ ትርጉም ያለው ተሳትፎ እንዲኖራቸው የማገዝ ሥራዎችን ጠቅሰዋል።
የሽግግር ፍትሕ ላይ ግንዛቤን ማሳደግ፣ የምርምር ሥራዎችን ማከናወንና የአፈጻጸሙን ሒደት መከታተል ከሚጠበቅባቸው ተግባራት መካከል እንደሆነ መግለጻቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡
የሽግግር ፍትሕ ሂደት ከሌሎች ሀገራት ተሞክሮ መማርን እንደሚጠይቅ ጠቁመው÷ የሀገሪቱን ታሪካዊ ሁኔታና ማኅበራዊ እውነታ ያገናዘበ አተገባበር ማስፈለጉን አስረድተዋል።