Fana: At a Speed of Life!

የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ከኢንተርፖል ጋር በመተባበር ተይዞ ወደ ሀገር እንዲመጣ የተደረገው አድነዉ ባሻዉ ለፍትህ ሚኒስቴር ተላለፈ

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 12፣ 2019 (ኤፍ ኤም ሲ) የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ከኢንተርፖል፣ ከROCK እና ከማላዊ ፖሊስ ጋር በመተባበር በሕገወጥ መንገድ ድንበር በማሻገር ወንጀል ተጠርጥሮ ከማላዊ ተይዞ ወደ ሀገር እንዲመጣ ባደረገው አድነዉ ባሻዉ ዉዳሞ እና በግብረ አበሩ ታምራት ኤርዳዶ ሞሎሮ ላይ ምርመራ አጣርቶ በማጠናቀቅ ለፍትህ ሚኒስቴር ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ አስተላልፏል።
‎
‎በቀረበው የክስ መዝገብ ዝርዝር መሠረት ተከሳሾቹ እነ አድነዉ ባሻዉ ዉዳሞ እና ታምራት ኤርዳዶ ሞሎሮ ሰዎችን ከኢትዮጵያ እስከ ደቡብ አፍሪካ ድረስ በሕገወጥ መንገድ ድንበር ለማሻገር የተደራጀ የወንጀል ቡድን መስርተው በዋና ወንጀል አድራጊነት በመምራት ተጎጂዎችን ከሀዋሳ እና ከሆሳዕና ከተሞች በማንሳት በሞያሌ፣ በኬንያ፣ በታንዛኒያ፣ በማላዊ፣ በዛምቢያ እና በሞዛምቢክ በኩል ድንበር የማሻገር የወንጀል ድርጊት ሲፈጽሙ እንደነበር በምርመራው እንደተደረሰበት ተገልጿል።

‎ተከሳሾቹ ሕገወጥ ጉዞውን ለማስፈጸም ከእያንዳንዱ ተጎጂ ከ400 ሺህ እስከ 1 ሚሊየን ብር የሚደርስ ከፍተኛ ገንዘብ በጥሬ እና በባንክ ሂሳብ ቁጥር ገቢ በማስደረግ መቀበላቸው እና የተጠየቁትን ገንዘብ በወቅቱ መክፈል ያልቻሉ ተጎጂዎችንና ቤተሰቦቻቸውን በኃይልና በዛቻ በማስጨነቅ ገንዘቡ እንዲከፈላቸው ሲያደርጉ መቆየታቸውን የፖሊስ የምርመራ መዝገብ አመላክቷል።
‎
‎ተጎጂዎች ያለበቂ ምግብና ውኃ ለብዙ ቀናት በእግር እንዲጓዙ ከመደረጋቸውም በላይ በደላሎችና በግብረ አበሮቻቸው በዱላ እየተደበደቡ ከፍተኛ አካላዊና ሥነ ልቦናዊ ስቃይ፣ ረሀብና እንግልት እንደደረሰባቸው ፖሊስ በምርመራ መዝገቡ ማረጋገጡን ጠቁሟል።
‎
‎ከዚህም ባሻገር ተከሳሾቹና ግብረ አበሮቻቸው ተጎጂዎችን ለሰው ማጓጓዣነት ባልተዘጋጁ አየር በሌላቸውና በጣም በተጨናነቁ ኮንቴነሮች፣ በቦቴ እና ሸራ በለበሱ ተሽከርካሪዎች በመጫን ለከፍተኛ የሕይወት አደጋ በሚያጋልጥ ሁኔታ ሲያጓጉዟቸው እንደነበርም በፖሊስ የምርመራ መዝገብ ተጠቅሷል።

በዚህም ምክንያት በርካታ ተጎጂዎች በዛምቢያ፣ በማላዊና በታንዛኒያ በሚገኙ ማረሚያ ቤቶች ውስጥ እስከ ሁለት ዓመት የሚደርስ የረጅም ጊዜ እስራትና እንግልት ማስተናገዳቸው ተገልጿል።

የፌደራል ዐቃቤ ሕግም ፖሊስ በተከሳሾቹ ላይ ሰፊ ማጣራት አድርጎ ባደራጀው መዝገብ ላይ ተመስርቶ ተጠርጣሪዎች ላይ 35 ክስ በመመስረት አሁን ላይ የወንጀል ጉዳዩ በመደበኛ ፍርድ ቤት እየታየ እንደሚገኝ የፌደራል ፖሊስ መረጃ ያመላክታል።

ዋና ተጠርጣሪ አድነው ባሻው የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ከኢንተርፖል፣ ከROCK እና ከማላዊ ፖሊስ ጋር በመተባበር ከማላዊ ተይዞ ወደ ሀገር እንዲመጣ መደረጉን ይታወሳል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.