የአባቶቹን ታሪክ ያስቀጠለው ክንደ ብርቱ ሠራዊት
አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 14፣ 2019 (ኤፍ ኤም ሲ) ኢትዮጵያ ከትውልድ ወደ ትውልድ ሲተላለፍ በመጣ የጀግንነት ታሪክ የምትታወቅ ሀገር ናት፡፡
ኢትዮጵያ በታሪካዊ ጠላቶቿ እንዲሁም በውጭ እና በውስጥ ሀይሎች ያልተፈተነችበት ጊዜ የለም፡፡ በተለይም ኢትዮጵያ ዳር ሉዓላዊነቷ እና ክብሯ እንዲደፈር እንዲሁም ደካማ ሀገር እንድትሆን ያልተደረገ ጥረት አልነበረም፡፡
ኢትዮጵያ በዘመናዊው የውትድርና ታሪክ በዓድዋ፣ በካራማራ፣ በጉራዕ፣ በጉንደትና በዶጋሊ ውጊያዎች ሉዓላዊነቷን ለመዳፈር የመጡ ወራሪዎችን አይቀጡ ቅጣት በመቅጣት የዓለም የነፃነት ታሪክን በወርቅ ቀለም ፅፋለች፡፡
በዚህም ኢትዮጵያ በድል አድርጊነት ሉዓላዊቷን እና ዳር ድንበሯን ከማስከበር ባለፈ ለሌሎች ሀገራት የነፃነት እና የአሸናፊነት ምሳሌ መሆን ችላለች፡፡
ኢትዮጵያውያን በውስጥ ልዩነቶቻቸው ሳይገደቡ፣ ሀገር ስትደፈር በአንድነት መቆም መቻላቸው እና ለሀገር ነፃነት ዘብ መቆማቸው የድላቸው ምስጢር እንደሆነም የታሪክ መዛግብት ያስረዳሉ፡፡
የነዛ ጀግኖች የታሪክ ባለአደራ የሆነው የሀገር መከላከያ ሠራዊት ከምንጊዜውም በላይ በዘመናዊ ቴክኖሎጂ፣ በአደረጃጀት፣ በተማረና በሠለጠነ የሰው ሀይል እና በሳይበር ምህዳር የበለጠ ራሱን አዘምኖ አደራጅቷል፡፡
በተለይም ሠራዊቱ ከባህላዊ የውጊያ ዘዴዎች በመውጣት የድሮን ቴክኖሎጂዎች፣ ዘመናዊ የመረጃ ሥርዓቶች፣ የዲጂታል ግንኙነት እንዲሁም የሳይበር ደኅንነት ሥርዓቶችን በመጠቀም አቅሙን አጠናክሯል።
ከእግረኛ ኃይሉ በተጨማሪ የአየር ኃይል፣ የባህር ኃይል እና የሳይበር ደኅንነት የሠራዊት ክፍሎች በአዲስ መልክ ተደራጅተው የዳበረ አቅም ለመፍጠር ተሰርቷል።
በዚህም ሠራዊቱ አሁን ላይ ልክ እንደ ዓድዋ፣ ካራማራ እና ሌሎች በርካታ ታሪካዊ የውጭ ወረራዎች ሀገሪቱን ለማፍረስ የመጡ ጠላቶችን በመመከት የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት እና ክብር እያስጠበቀ ይገኛል፡፡
ከዚህም በተጨማሪ የታሪካዊ ጠላቶች ተላላኪ የሆኑ የውስጥ ባንዳዎችን ተልዕኮ በማክሸፍ የሀገር አለኝታና ዘብ ሆኖ ግዳጁን እየተወጣ ነው።
ከሀገር ሉዓላዊነት ባለፈ ሠራዊቱ የአባቶቹን የሰላም አስከባሪነት ታሪክ በመከተል በዓለም አቀፍ ሽብርተኝነትን በመከላከል የሰላም ተልዕኮውን በብቃት እየተወጣ ይገኛል፡፡
በሚኪያስ አየለ