ለሀገር ክብር የቆመው – የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት
አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 15፣ 2019 (ኤፍ ኤም ሲ) የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት አደጋ ላይ ሊጥሉ የተሞከሩ ሙከራዎች ነበሩ፡፡ በዚህ ጊዜ ታድያ የክተት አዋጅ ይታወጃል፤ የኢትዮጵያ ህዝብም “ሆ” ብሎ ሀገሩን ለመጠበቅ ወኔን ተላብሶ ይወጣል፡፡
ዛሬ ላይ ዝግጁ ሆኖ፣ ራሱን በቴክኖሎጂና ዘመናዊነት አብቅቶ በተጠንቀቅ የሚጠብቅ የሀገር መከላከያ ሠራዊት ያላት ሀገር ናት ኢትዮጵያ፡፡
የመከላከያ ሠራዊት 1900 ዓ.ም ላይ የሀገሪቱን ሉዓላዊነት በተቋም ደረጃ የሚያስጠብቅ ሆኖ እንዲመሰረት ሆኗል፡፡ የመጀመሪያው የጦር ሚኒስትር ፊታውራሪ ሀብተጊዮርጊስ ዲነግዴም በጥቅምት 15 ቀን ተሹመዋል፡፡
የመከላከያ ሠራዊት ቀን በዚህ በጥቅምት 15 ቀን እንዲከበር የተደረገውም በዚህ የታሪክ ትስስር መነሻነትና ለሠራዊቱ የገባውን ክብር ለመስጠትም በማለም ነው፡፡
ወታደር የሀገሩን ዳር ድንበር ለማስጠበቅ የራሱን ህይወት ጥሎ፣ ቤተሰቦቹን ወዳጆቹን ሁሉ ትቶ ሀገሩን አስቀድሞ ዳር ድንበሯ ሊጠብቅ ወቶ የሚያድር ነው፡፡
በፌደራል ነጋሪት ጋዜጣ ላይ ከተቀመጡት የመከላከያ ሠራዊት ተልዕኮዎች መካከል ሀገሪቱንና ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቱን ከውጭ ወራሪ ኃይሎች፣ ሽብርተኞችና ከውስጥ ፀረ-ሠላም ኃይሎች በአስተማማኝ ሁኔታ በመከላከል የሀገሪቱ ሠላም እንዲጠበቅና የፈጣን ልማትና የዲሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ እንቅስቃሴ ያለ እንቅፋት እንዲቀጥል ማድረግ አንዱ ነው፡፡
እንዲሁም ሀገራዊ ደህንነትን ማረጋገጥና በከባቢያዊ፣ አህጉራዊና ዓለም አቀፋዊ የሠላም ማስከበር ተልዕኮዎች ላይ በብቃት መሳተፍ የሚጠቀሱ ናቸው፡፡
የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት የህዝብን ሰላም ማስጠበቅ፣ የሀገርን ዳር ድንበር ከማስከበር ባሻገር ኢትዮጵያን ወክሎ ለተለያዩ ሀገራት ሰላም መረጋገጥ አስተዋፅኦን ሲያደርግ መቆየቱ የዛሬ ማንነቱ ብቻ አይደለም፡፡
በኮሪያና በኮንጎ የሰላም ማስከበር ተልዕኮዎች ኢትዮጵያ ትልቅ አስተዋጽኦን አበርክታለች፤ ለአብነትም በአይበገሬነቱ የሚታወቀውን፣ ብቸኛዋ አፍሪካዊት ሀገር ኢትዮጵያ ተልኮ በኮሪያ የዘመተውን የቃኘው ሻለቃ ክፍለ ጦር ማንሳት ይቻላል፡፡
በቅርብ ጊዜያትም በሩዋንዳና ቡሩንዲ፣ በላይቤሪያ፣ በሱዳን ዳርፉር፣ በአቢዬ(UNISFA)፣ በሶማሊያ (AMISOM)፣ በደቡብ ሱዳን (UNMISS) የሰላም ማስከበር ተልዕኮዎችን ተወጥቷል፡፡ ከዚህም ባሻገር በዲሲፕሊንና ከህዝብ ጋር ባለው ሰብዓዊ ቀረቤታ የሚነሳ ሆኗል፡፡
ነፃነትን በደሙ የገዛ ህዝብ አካል የሆነው የመከላከያ ሠራዊት የሌሎችን ነጻነትና ደህንነት ለማስከበር መስራቱ የሚጠበቅ ተግባር ነው፡፡
የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ለዚህ የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት በሰላም ማስከበር ተግባራት ላይ ለሚያደርገው አስተዋጽኦና ለሰላም ላለው ቁርጠኝነት እውቅናን ሰጥቷል፡፡
ይህ ተቋም ግዙፍ ተቋም ነው ፤ ትልቅ ታሪኩን አስጠብቆ በሪፎርም ራሱን አዘምኖ፣ ዛሬ ላይ መሳሪያዎችን በራሱ በማምረት፣ ከሀገር አልፎ ለቀጣናው ዘብ የመሆን አቅምን አጎልብቷል፤ ለማንኛውም አይነት ተልዕኮዎች ዝግጁነቱን በማሳየት መከታ መሆኑን አስመስክሯል፡፡
119ኛው የመከላከያ ሠራዊት ቀን “የድል ሠራዊት” በሚል መሪ ቃል በዛሬው ዕለት እየተከበረ ይገኛል።
#ኢትዮጵያ #ትልቅሀገር #ትልቅሕዝብ #ታላቅርዕይ
በቤተልሔም ግርማ