አዲስ አበባን ለነዋሪዎቿ የተሻለ ኑሮ የምትፈጥር ከተማ እናደርጋታለን – ከንቲባ አዳነች አቤቤ
አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 15፣ 2019 (ኤፍ ኤም ሲ) አዲስ አበባን ለነዋሪዎቿ የተሻለ ኑሮ የምትፈጥር ከተማ እናደርጋታለን አሉ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ።
የእንጦጦ ፒኮክ የወንዝ ዳርቻ ልማት አካል የሆነው የቀጨኔ–አምባሳደር–ጊዮን-ኢሬቻ–ባምቢስ የወንዝ ዳርቻ ልማት በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የመርቆ ለአገልግሎት ክፍት ሆኗል።
ከንቲባዋ በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው ባስተላለፉት መልዕክት፤ ታላቅ ልማት የአዲስ አበባን ውበት፣ የነዋሪዎቿን የኑሮ ጥራት፣ የከተማዋን የቱሪዝም መዳረሻነትና የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ የሚያሳድግ ወሳኝ ሥራ ነው ብለዋል፡፡
የወንዝ ዳርቻዎችን ከብክለት፣ ከተፈጥሮ መራቆትና ከአደጋ ተጋላጭነት በማውጣት፤ ለአረንጓዴ ልማት፣ ለመዝናኛ፣ ለስፖርት፣ ለንግድና ለማኅበራዊ ትስስር ምቹ ስፍራዎች እየተፈጠሩ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
ሥራው የወንዞችን ተፈጥሯዊ ይዘት ከመመለስ ባለፈ፣ ከተማዋን ለነዋሪዎቿ የበለጠ ምቹ፣ ማራኪና ለኑሮ የተሻለች እያደረጋት እንደሚገኝ አስገንዝበዋል፡፡
የልማቱ ዋና ዓላማ ውብ ስፍራዎችን መገንባት ብቻ ሳይሆን ለነዋሪዎች ጤናማ አካባቢ፣ የመዝናኛ አማራጭና የኢኮኖሚ ዕድሎች መፍጠር ነው ብለዋል፡፡
ይህ የጋራ ሀብት በንፅህና እንዲጠበቅና የተገነቡ መሠረተ ልማቶች በአግባቡ እንዲያገለግሉ ሁሉም የድርሻውን እንዲወጣም አስገንዝበዋል፡፡