አዲስ ገጽታ
አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 15፣ 2019 (ኤፍ ኤም ሲ) መንግሥት ሁለንተናዊ ብልጽግናን ለማረጋገጥ እና የሕዝብን የኑሮ ደረጃ ከፍ ለማድረግ በሚታደርገው ሀገራዊ ጥረት የከተሞች ልማትን ከሥነ-ምህዳር ጥበቃ እና ከኢኮኖሚ እድገት ጋር በማቀናጀት በተግባር እያስመሰከረ ይገኛል።
የአፍሪካ የዲፕሎማሲ መዲና የሆነችው አዲስ አበባ በዚህ ረገድ ራሷን በዘመናዊነትና በአረንጓዴ ልማት የመቀየር ታላቅ ታሪካዊ ምዕራፍ ላይ ትገኛለች።
የመደመር መንግሥት ከተማዋን ለነዋሪዎቿ ምቹ፣ ለቱሪስቶች ማራኪ እና ለዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ደግሞ የስማርት ከተማ አርአያ ለማድረግ የወጠነው ርዕይ በተግባር እየታየም ይገኛል።
በዛሬው ዕለት በይፋ ለአገልግሎት የበቃው የቀጨኔ–አምባሳደር–ጊዮን–ኢሬቻ–ባምቢስ የወንዝ ዳርቻ ልማት ፕሮጀክትም አዲስ አበባን የስነ-ምህዳር መናኸሪያ እና የዘመናዊ ሕይወት መገለጫ ማድረጓን የሚያረጋግጥ ግዙፍ ማሳያ ነው።
ከቀጨኔ በአምባሳደር እና በኢሬቻ በኩል እስከ ባምቢስ የተዘረጋው ይህ ፕሮጀክት 351 ሄክታር አጠቃላይ ስፋት እና 10 ኪሎ ሜትር ርዝመት ያለው ሲሆን፣ የከተማዋን ነዋሪዎች የዕለት ተዕለት ኑሮ ምቹ ከማድረግ በተጨማሪ አካባቢያዊ ሚዛኑን የጠበቀ ገጽታን ገንብቷል።
የተፈጥሮና የአካባቢ ጥበቃን በተመለከተ የአፈርና ውሃ ጥበቃ ሥራዎች፣ የወንዝ ማጽዳት፣ የጎርፍ መከላከል፣ እንዲሁም ሰፊ የአረንጓዴ ስፍራዎችን ማስፋፋትና የገጽታ ማስዋብ ሥራዎች ተከናውነዋል።
ከዚህ ጎን ለጎን 16 ኪሎ ሜትር አዲስ የአስፋልት መንገድ፣ 20 ኪሎ ሜትር የብስክሌት መንገድ፣ 22 ኪሎ ሜትር የእግረኛ መንገድ እና 5 ኪሎ ሜትር የመሮጫ ትራክን ጨምሮ 18 የተሽከርካሪ እና 23 የእግረኛ ድልድዮች ተገንብተዋል።
ለስፖርት፣ ለመዝናኛና ለማኅበራዊ ትስስር 12 የስፖርትና የጤና ማዕከላት፣ 21 የሕፃናት መጫወቻ ስፍራዎች፣ 15 ፕላዛዎችና አምፊ ቲያትሮች፣ እንዲሁም 8 የውሃ ትርዒት ማሳያዎች ለአገልግሎት ዝግጁ ሆነዋል። የኢኮኖሚና የሥራ ዕድል ፈጠራን በተመለከተ ለወጣቶች የሥራ ዕድል ለመፍጠር 30 ካፌዎች፣ 185 ሱቆች እና የባንክ አገልግሎቶች ተካተዋል።
ከዚህም በላይ ቀደም ሲል በወንዝ ዳርቻው ይኖሩ ለነበሩ ነዋሪዎች የዕደ ጥበብ ምርቶች ማምረቻ፣ ማሳያና መሸጫ ማዕከል እንዲሁም የግብርና ምርቶችን በቀጥታ ማቅረቢያና መሸጫ ማዕከል ተዘጋጅቷል።
በተጨማሪም የአየር ንብረት ለውጥን ለመቋቋም የሚያስችሉ 22 የመኪና ማቆሚያ ስፍራዎች፣ የንጹህ ውሃ፣ የፍሳሽና የጎርፍ ማስወገጃ መስመሮች፣ እንዲሁም በአንድ ጊዜ ከ100 በላይ መኪናዎችን ቻርጅ ማድረግ የሚችሉ 8 የኤሌክትሪክ መኪና ቻርጅ ማድረጊያ ማዕከላት ተዘርግተዋል።
ይህ ፕሮጀክት የከተማ መሠረተ ልማትን ከዘመናዊ የኑሮ ከባቢ ጋር በማቀናጀት ለነዋሪዎች ምቹና የኢኮኖሚ አቅም ያለው ከባቢን የፈጠረ ስኬታማ የልማት ምዕራፍ ነው።
#ኢትዮጵያ #ትልቅሀገር #ትልቅሕዝብ #ታላቅርዕይ