Fana: At a Speed of Life!

ለጎንደር ብስራት – የመገጭ ተስፋና ትንሣኤ

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 15፣ 2019 (ኤፍ ኤም ሲ) በኢትዮጵያ ታሪክ ስሟ በደመቀውና የኪነ-ሕንጻ ጥበብ ማማ በሆነችው ታሪካዊቷ የጎንደር ከተማ ዙሪያ፣ ለዘመናት በሰዎች አንደበት የሚመላለስ አንድ አጉል የሥነ-ቃል ተረትና ምሳሌ ነበረ።

በተለይም ላለፉት አሥራ ዘጠኝ ዓመታት የከተማዋንና የአካባቢውን ሕዝብ የውኃ ጥምና የልማት ተስፋ አግቶ የቆየው የመገጭ ፕሮጀክት ሲነሳ ነዋሪው በምሬት “እንደ መገጭ ግድብ ቆመህ ቅር!” ይል ነበር፡፡

ይህ አባባል የቀልድ አልነበረም፤ ይልቁንም አራት የአገር መሪዎች የተፈራረቁበት፣ ሰባት የክልል ፕሬዚዳንቶችና አሥራ ሁለት ከንቲባዎች ሳይጨርሱት ያለፈው፣ የተንቀራፈፈ አሠራርና የተስፋ መቁረጥ መግለጫ የነበረ “የልማት እርግማን” ነበረ።

መገጭ ወንዝ በፋሲለደስ ዘመን የተገነቡ ታሪካዊ ድልድዮችን ተሸክሞ ለዘመናት ቢፈስም፣ ዘመናዊው ግድቡ ግን ተጀምሮ የማያልቅ  የቆሞ-ቀሪነት ተምሳሌት ሆኖ ቆይቶ ነበር።

ይህንን ለ19 ዓመታት የዘለቀ እና አጠቃላይ ወጪው የዋጋ ንረትን ጨምሮ ከ17 እስከ 20 ነጥብ 7 ቢሊየን ብር ያባከነ ፕሮጀክት ወደ ፍጻሜ ለማምጣት የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) አስተዳደር ቁርጠኛ አመራር አስፈልጓል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ አገራዊ ሜጋ ፕሮጀክቶችን ከመጀመር ባለፈ “የመደመር እሳቤን” መሠረት በማድረግ ለፍሬ ማብቃት የለመደ እጃቸውን ወደ መገጭ ዘረጉ።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ “ሕዝቡ በውኃ እጥረት እየተቸገረ አንድ ፕሮጀክት ለዓመታት አለመጨረስ እርግማን ነበር” በማለት የችግሩን ስር የሰደደ መልክ ገልጸውታል፡፡  ፕሮጀክቱን ሲያጓትት የነበረውን ሥራ ተቋራጭ  በመቀየር ጥብቅ የማስተካከያ እርምጃ ወሰዱ። በግላቸው የቅርብ ክትትልና አዲስ የፈረቃ አሠራር አቅጣጫ በመስጠት፣ ለ18 ዓመታት የሞተ መስሎ የቆየውን ግድብ በአስደናቂ ፍጥነት በ2 ዓመታት ውስጥ ብቻ አጠናቀው በጥቅምት 2019 ዓ.ም ለምረቃ አበቁት። ይህ ስኬት የተቋረጠ ሕልም እንደገና ሊነሳ እንደሚችል እና የዘገየ የልማት ራዕይ በጽናት ወደ ፍጻሜ እንደሚደርስ ያሳየ የሀገር በቀል አቅም ማሳያ ሆኗል።

ዛሬ በጥቅምት የመገጭ ወንዝ እሮሮ ታሪክ ተቀልብሶ አዲስ ምዕራፍ ሲበሰር የጎንደር ሕዝብ የነበረው የትናንት እርግማን ተረት እንዲቀር አድርጎታል።

ከ185 ሚሊየን ሜትር ኩብ በላይ ውኃ የመያዝ አቅም ያለው ይህ ግዙፍ ግድብ፣ ዘመናዊ የውኃ ማጣሪያና ማሰራጫ መስመሮችን በመጠቀም የታሪካዊቷን የጎንደር ከተማና የአካባቢዋን ነዋሪዎች የዘመናት የንጹሕ መጠጥ ውኃ ጥያቄ በዘላቂነት ለመፍታት የሚያስችል ነው።

ከዚህ ባሻገር ከዝናብ ጥገኝነት በመውጣት ከ17 ሺህ ሔክታር በላይ መሬትን በመስኖ በማልማት፣ በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ አርሶ አደሮችን በቀጥታ ተጠቃሚ ያደርጋል። ይህም በዓመት እስከ ሦስት ጊዜ በማምረት ለአካባቢው የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ ከፍተኛ እገዛ ያደርጋል።

በግድቡ የተፈጠረው ግዙፍ ሰው-ሠራሽ ሐይቅ ልክ እንደ “ጎርጎራ ፕሮጀክት” ሁሉ ለአካባቢው ወጣቶች ሰፊ የሥራ ዕድል የሚፈጥሩ የዓሣ እርባታዎችን፣ የከተማ ግብርናንና የቱሪዝም ሪዞርቶችን በመሳብ አዲስ የኢኮኖሚ መነቃቃትን ይፈጥራል።

አሁን መገጭ ከእርግማንና እሮሮ ወጥቶ ለጎንደርና አካባቢዋ አዲስ የልማት እና ብልፅግና ምዕራፍ የሚከፍት ታሪካዊ ፕሮጀክት ሆኗል፡፡

በጸጋ ታሪኩ

 

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.