የኅብረ ብሔራዊነት ማሳያ፤ የሀገር መከላከያ ሠራዊት
አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 18፣ 2019 (ኤፍ ኤም ሲ) የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት የሀገርን ሉዓላዊነትና አንድነት ከማስከበር ባለፈ፤ የኅብረ ብሔራዊነት ህያው ምስክር ነው።
ይህ ሠራዊት ባለፉት ዘመናት አደረጃጀቱና ዘመናዊነቱ ቢቀያየርም፤ አንድ የማይለወጥ መሠረታዊ መለያ አለው፡፡ እሱም ከተለያዩ ብሔሮች ብሔረሰቦች የተወጣጡ ውድ ልጆችን በአንድ ዓላማ አስተሳስሮ የሀገርን ዳር ድንበር ማስከበሩ ነው።
ሠራዊቱ የኢትዮጵያን ብዝሃነት ወደ አንድ ታላቅ ኃይል በመለወጥ ረገድ የረጅም ዘመን ታሪካዊ መሠረት አለው። የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ባለፉት ሦስት አሥርት ዓመታት ውስጥ የተለያዩ ተቋማዊ ሪፎርሞችንና የማሻሻያ ሥራዎችን አሳልፏል።
በአሁኑ ወቅት ሠራዊቱ በሕገ መንግሥቱ መሠረት ከማንኛውም የፖለቲካ ወገንተኝነት ነጻ ሆኖ፤ የሁሉንም ብሔሮች ብሔረሰቦች ውክልና ባረጋገጠ መልኩ የተገነባ ተቋም ነው።
የሀገር መከላከያ ሠራዊት የጦር ግንባር ተዋጊ ብቻ ሳይሆን፤ የኢትዮጵያ አንድነት፣ ወንድማማችነትና የኅብረ ብሔራዊነት ዓርማ ነው። የሠራዊቱ ኅብረ ብሔራዊነት የኢትዮጵያን ሰላም ዘላቂ የሚያደርግ፣ ብዝሃነትን የሚያስውብና ለነገዋ የበለጸገች ኢትዮጵያ መሠረት የሚጥል ነው።
ከተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች የመጡ፣ የተለያዩ ቋንቋዎችን የሚናገሩና የተለያየ ባህል ያላቸው በአንድ የጋራ ዓላማ በሀገር ፍቅር ተሳስረው ይቆማሉ። ይህ የሚያሳየው ሠራዊቱ ከሕዝብ የወጣና ለሕዝብ የሚኖር፣ የሕዝብ የኩራት ምንጭ መሆኑን ነው።
የመከላከያ ሠራዊት ጥንካሬ ምንጭ የጦር መሣሪያ ዘመናዊነት ብቻ ሳይሆን በውስጡ የያዘው የሕዝቦች አንድነት ነው።
አሁን ላይም ሠራዊቱ ከሁሉም የሀገሪቱ ማዕዘናት የተወጣጡ ውድ ልጆችን በአንድ ዓላማና በአንድ የኢትዮጵያዊነት መንፈስ በማሰለፍ የሀገርን ዳር ድንበር በጽናት እየጠበቀ ይገኛል። የኢትዮጰያ መከላከያ ሠራዊት ታሪክ የነጻነት፣ የሉዓላዊነትና የጽናት ታሪክ ነጸብራቅ ነው፡፡