Fana: At a Speed of Life!

ኢትዮጵያና ሩሲያ በኢነርጂ ዘርፍ

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 18፣ 2019 (ኤፍ ኤም ሲ) ኢትዮጵያ እና ሩሲያ በኢነርጂ ዘርፍ በተለይም የሰላማዊ ኒውክሌር ቴክኖሎጂ ልማት እና የቁጥጥር ማዕቀፎችን በመዘርጋት ረገድ የጠበቀ ትብብር እያደረጉ ይገኛሉ።
ኢትዮጵያ ለኢነርጂ ዘርፍ ሰፊ ትኩረት ሰጥታ እየሰራች ሲሆን፤ ዘርፉ የሀገሪቱን አጠቃላይ ኢኮኖሚ፣ የኢንዱስትሪ ልማትና የቀጣናዊ የኃይል ትስስር ማጠናከሪያ ምሰሶ ሆኗል፡፡
ኢትዮጵያ የኒውክሌር ኃይልን እንደ አማራጭ የኢነርጂ ዘርፍ ለመጠቀም ስትራቴጂካዊ ርምጃዎችን በመውሰድ ላይ ትገኛለች።
በአሁኑ ወቅት የሀገሪቱ የኃይል አቅርቦት 90 በመቶ ገደማ በውኃ ኃይል ላይ የተመሠረተ በመሆኑ፤ በአየር ንብረት ለውጥና በድርቅ ምክንያት የሚመጣን የኃይል መቆራረጥ ስጋት ለመቀነስ የኒውክሌር ኢነርጂ እንደ ዋነኛ አማራጭ ተወስዷል፡፡
የኒውክሌር ኢነርጂ አማራጭን ወደ ተግባር ለመቀየር ኢትዮጵያ የኒውክሌር ኮሚሽን በማቋቋም ከተለያዩ ሀገራት ጋር የትብብር ስምምነቶችን የፈፀመች ሲሆን ሩሲያ የኢትዮጵያ ቀደሚዋ የኢነርጂ ዘርፍ አጋር ሆናለች፡፡
ይህ በኢትዮጵያና በሩሲያው ሮሳቶም መካከል እየተከናወነ ያለው ታላቅ የኢነርጂ ትብብር ኢትዮጵያን በምሥራቅ አፍሪካ ቀጣናዊ የኒውክሌር ኃይል መሪ ለማድረግ የሚያስችል ስትራቴጂካዊ ርምጃ ነው።
በዚህም ኢትዮጵያ ከሩሲያው የመንግሥት የኒውክሌር ኮርፖሬሽን ‘ሮሳቶም’ ጋር በትብብር ለመስራት የተስማማች ሲሆን ተቋሙ በኢትዮጵያ የመጀመሪያውን ሰላማዊ ኒውክሌር ኃይል ማመንጫ ለመገንባት በሚደረግው ጥረት ውስጥ ድጋፍ እያደረገ ይገኛል፡፡
በተጨማሪም ከ2032 እስከ 2034 ባሉት ዓመታት ውስጥ በኢትዮጵያ ሙሉ በሙሉ ተገንብተው ስራ እንደሚጀምሩ በሚጠበቁት የኃይል ማመንጫዎች ውስጥ ሮሳቶም ለኢትዮጵያውያን የዘርፉ ባለሙያዎች ሰፊ የትምህርትና የሥልጠና ድጋፍ ያደርጋል።
የሩሲያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሰርጌይ ላቭሮቭ ከ3ኛው የሩሲያ አፍሪካ ጉባኤ በፊት ከጋዜጠኛች ጋር በነበራቸው ቆይታ÷ ሩሲያ ዓለም አቀፍ ሕጎችን መሠረት በማድረግ የኢትዮጵያን ሰላማዊ የኒውክሌር ልማት እየደገፈች ትገኛለች ብለዋል፡፡
ከኢትዮጵያ ጋር በሰላማዊ የኒውክሌር ልማት ላይ በተጀመረው ትብብር የኢትዮጵያውያን ባለሙያዎችን አቅም ማብቃት ትኩረት የተሰጠው ዋና ጉዳይ መሆኑንም ተናግረዋል።
በሞስኮ በሚካሄደው 3ኛው የሩሲያ-አፍሪካ ጉባኤ የኢነርጂ ትብብርን ጨምሮ በዲጂታል ቴክኖሎጂ፣ አርቴፊሻል ኢንተለጀንስ እና በንግድ ጉዳዮች ላይ የኢትዮጵያና የሩሲያ ልዑካን ውይይት ያደርጋሉ ተብሎም ይጠበቃል፡፡
በሚኪያስ አየለ
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.