የምንገነባት አዲስ አበባ ነዋሪዎቿን በእኩል የልማት ተጠቃሚ የምታደርግ እንድትሆን ቁርጠኛ ነን – ከንቲባ አዳነች አቤቤ
አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 22፣ 2019 (ኤፍ ኤም ሲ)የምንገነባት አዲስ አበባ ነዋሪዎቿን በእኩል የልማት ተጠቃሚ የምታደርግ ከተማ እንድትሆን ቁርጠኛ ነን አሉ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ፡፡
ከንቲባ አዳነች አቤቤ በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው ባሰፈሩት መልዕክት፤ ዛሬ የቦሌ ሹቡ ኤጀርሳ የተቀናጀ የነዋሪዎች መንደርን መርቀን ለአካባቢው የልማት ተነሺዎች አስረክበናል ብለዋል።
የቦሌ ሹቡ ኤጀርሳ የተቀናጀ የነዋሪዎች መንደር የሰው ተኮር ልማት በተግባር የተረጋገጠበት ነው ሲሉም ጠቁመዋል፡፡
የከተማ ልማት ዋነኛ ዓላማ መሠረተ ልማትን መገንባት ብቻ ሳይሆን፤ የዜጎችን ኑሮ ማሻሻል፣ መብትና ጥቅም ማስጠበቅ እና የተሻለ የኑሮ ዕድል መፍጠር መሆኑንም ገልጸዋል፡፡
በአዲስ አበባ እየተገነባ የሚገኘው የሰው ሠራሽ አስተውሎት ዩኒቨርሲቲ የሀገራችንን የቴክኖሎጂና የኢኮኖሚ እድገት የሚያፋጥን ትልቅ ሀገራዊ ፕሮጀክት ነው ብለዋል።
ሆኖም ፕሮጀክቱ ቀደም ሲል መሬቱን ለእርሻ፣ ለግጦሽና ለመኖሪያነት ሲጠቀሙ የነበሩ አርሶ አደሮችን ሕይወት የሚነካ በመሆኑ የልማቱ ተጠቃሚ እንጂ ተጎጂ እንዳይሆኑ ልዩ ትኩረት መሰጠቱን አመልክተዋል።
በዚህም መሠረት ለሰው ሠራሽ አስተውሎት ዩኒቨርሲቲ ልማት ከእርሻና መኖሪያ ቦታቸው ተነሺ ለሆኑ የቦሌ ሹቡ ኤጀርሳ አርሶ አደሮች የተቀናጀ መኖሪያ መንደር ገንብተን፣ የኑሮና የገቢ ምንጮቻቸውን የሚያሳድጉ አቅርቦቶችንም አካተናል ነው ያሉት፡፡
ይህም የነዋሪዎቹን ማኅበራዊ ትስስር ጠብቆ ወደ ተሻለ የአኗኗር ሁኔታ የሚያሸጋግር ሰው ተኮር የልማት አሠራር መሆኑን አስረድተዋል።
ልማት ማለት ሰውን ከነበረበት ቦታ ማንሳት ብቻ ሳይሆን የኑሮ ደረጃውን ማሻሻል፣ የኢኮኖሚ አቅሙን ማጠናከርና የነገ ተስፋውን ማለምለም ጭምር መሆኑንም አብራርተዋል።
የአካባቢው ነዋሪዎች ቦታው ለታላቅ ሀገራዊ ፋይዳ እንደሚውል ስናስረዳቸው ዩኒቨርቲው ለልጆቻቸው የመማር ዕድልና የሀገርን በዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ የመሆን አቅም እንደሚፈጥር በመገንዘብ በፈቃደኝነት ትብብራቸውን ማድረጋቸውን ጠቁመው ምስጋናቸውን አቅርበዋል፡፡
ይህ ተግባር በመደመርና በትብብር ስንንቀሳቀስ ሁሉንም ወገኖች ተጠቃሚ ማድረግና ዘላቂ ልማትን ማረጋገጥ እንደምንችል ማሳያ ነው ያሉ ሲሆን የቦሌ ሹቡ ኤጀርሳ ነዋሪዎች መንደር ይህንኑ ሰው ተኮር የልማት አቅጣጫችንን በተግባር የሚያሳይ ምሳሌ ነው ብለዋል።
የምንገነባት አዲስ አበባ የሁሉም ነዋሪዎቿን ክብር፣ መብትና ጥቅም የምታስጠብቅ፣ ሁሉንም በእኩል የልማት ተጠቃሚ የምታደርግ ከተማ እንድትሆን ቁርጠኛ ነን ሲሉም አጽንኦት ሰጥተዋል።