Fana: At a Speed of Life!

ርዕይን በዲሲፕሊን መቅረጽ፡ ከሁርሶ እስከ ሀገር ግንባታ

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 21፣ 2019 (ኤፍ ኤም ሲ) የሀገር ግንባታ ሂደት የፖሊሲ ማዕቀፎችን ብቻ ሳይሆን እነዚያን ርዕዮች ወደ መሬት አውርዶ ሕዝብን የማስተባበር አቅም ያለው የሰው ሀብት ልዕልና የሚጠይቅ ታላቅ ሀገራዊ ተልዕኮ ነው።
ዛሬ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የመደመር መንግሥት አመራሮች በሁርሶ ወታደራዊ ማሠልጠኛ ማዕከል ሥልጠና በመውሰድ ላይ እንደሚገኙ በመልዕክታቸው አጋርተዋል።
ለመሆኑ ይህ የአመራሮች ስልጠና ወታደራዊ ሥልጠና ለጦር ግንባር ብቻ ነው? ወይስ ሀገርን ለመምራትም ትልቅ ትምህርት አለው?
የጠቅላይ ሚኒስትሩ መልዕክት የሚያነሳው ይህንኑ ጉዳይ ነው። እንደ እሳቸው ገለጻ፣ የኢትዮጵያን ሥልጣኔ ለመገንባት ቁሳዊ፣ መንፈሳዊ፣ ባህላዊና ሞራላዊ ብልጽግናን በአንድነት ማረጋገጥ ያስፈልጋል።
ለዚህም በዕውቀት፣ በሥነ ምግባርና በአካል የተዘጋጀ አመራር ወሳኝ ነው።
ለአመራሮቹ እየተሰጠ ያለው ስልጠና የዘመኑን ተለዋዋጭ ጂኦፖለቲካዊ እና ማህበራዊ ጫናዎች ለመቋቋም የሚያስችል ስትራቴጂካዊ ርምጃ ነው።
የኢትዮጵያን ታሪካዊ ሥልጣኔ ዳግም ለማንቃት የሚደረገው ጥረት በቁሳዊ ዕድገት ብቻ ሊወሰን አይችልም።
በመሆኑም በአካል የዳበረ፣ በሞራል የጠነከረ፣ በዕውቀት የተሳለና በጥበብ የበሰለ አመራር በማሰልጠን ሁለንተናዊ ብልጽግናን ማረጋገጥ ይቻላል።
“ወታደሮች ዒላማ፤ ሲቪሎች ደግሞ ዓላማ አላቸው፤ የሁለቱም ግብ ድልን ማስመዝገብ ነው” የሚለው የጠቅላይ ሚኒስትሩ ሐሳብ፤ ዒላማውንም የሚመታ፣ ዓላማውንም የሚያሳካ አመራር ለመፍጠር ወሳኝ ውህደት ለመሆኑ በቂ ማብራሪያ ይሰጣል።
በዚህ ረገድ እንደ ሲንጋፖር፣ አሜሪካ፣ ስዊዘርላንድ፣ እስራኤል፣ ቻይና እና ሌሎች ሀገሮች አመራሮቻቸውን የማሰልጠን ልምድ አላቸው።
ወታደራዊ ዲሲፕሊንና ሳይንስን ከሲቪል አስተዳደር ጋር ማጣመር ታላላቅ ሀገራት ተቋሞቻቸውን ለማጠናከር የተጠቀሙበት የብልህ መንገድ ነው።
በኢትዮጵያም እየተሰጠ ያለው ስልጠና አመራሩን ከቢሮክራሲያዊ መዘግየትና ከቸልተኝነት ነፃ አውጥቶ፣ ሀገራዊ ርዕይን ከግብ ጋር በማጣጣም ውጤታማ የሀገር ግንባታ ኃይል ለማድረግ ያለመ ነው።
በሶስና አለማየሁ
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.