ታሪክ የማይረሳው ክህደት
አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 24፣ 2019 (ኤፍ ኤም ሲ) ሕገ ወጡ ህወሓት በኢትዮጵያ ታሪክ ትልቅ ቦታ ያለውን የትግራይ ሕዝብ ፈፅሞ መወከል የማይችል ለራሱ ጥቅም የተሰባሰበ ቡድን ነው፡፡
የህወሓት ሕገ ወጥ ቡድን የመንግሥት ሥልጣንን ተቆጣጥሮ በነበረበት ዓመታት በበርካታ ወገኖች እና ተቋማት ላይ ታሪክ የማይሽረው ጥፋቶችን የፈፀመ ሲሆን÷ ዜጎችን ለከፋ ሰብዓዊ መብት ረገጣ ፤ ሀገሪቱንም ለኢኮኖሚያዊ፣ ማኅበራዊ እና ፖለቲካዊ ቀውስ ዳርጓል።
ህወሓት ለራሱ ጥቅም ሲል የሰውን ሕይወት እንደሚያጠፋ፣ የሕዝብን ሰላም እንደሚረብሽ እና ከሕዝብ ይልቅ የራሱን ቡድን ፍላጎት እንደሚያስቀድም ይታወቃል፡፡
ቡድኑ ከትግራይ ሕዝብ ይልቅ የራሱን ሥልጣንና ጥቅም ለማቆየት በስልጣን ዘመኑ፣ ከስልጣን ከተገለለ በኋላ እንዲሁም አሁን ላይ እያደረገ ባለው እንቅስቃሴ በርካታ ሰብዓዊ ግፎችን እና ሀገር አፍራሽ ተግባራትን ሲፈፅም ቆይቷል፡፡
ቡድኑ በሕዝብ ተገፍቶ ያጣውን ስልጣን ለማቆየት አላማ ቢስ ግጭቶችን ሲያስነሳ፣ ሰዎችን ሲግድል፣ ሲያፍን እንዲሁም በጋራ የኖሩ ሕዝቦችን በመነጣጠል ለዘመናት የሴራ ፖለቲካውን ሲያራምድ ቆይቷል፡፡
በተለይም ቡድኑ ከስልጣን ከተወገደ እና መቐለ ከመሸገ በኋላ የሰሜን ዕዝን በመክዳት ጥቅምት 24 ቀን 2013 ዓ.ም የኢትዮጵያ ሕዝብ ጋሻ እና መከታ በሆነው መከላከያ ሠራዊት ላይ የፈፀመው ጥቃት መላው ኢትዮጵያውያንን ያሳዘነ ድርጊት መሆኑ አይዘነጋም።
የሰሜን ዕዝ ለህዝብና ለሀገር በሙሉ ዕምነትና ፅናት በትግራይ ክልል ግዳጁን በመወጣት ላይ በነበረበትና ህዝባዊነቱን አጉልቶ እየሰራ ባለበት ወቅት የተፈፀመበት በደልና ክህደት ታሪክ መቼም አይረሳውም።
ሠራዊቱ ከ20 ዓመታት በላይ በትግራይ ክልል ያከናወናቸውን በጎ ተግባሮች እና ድጋፎች የካደው ይህ የህገ ወጡ ህወሓት ድርጊት የቡድኑን ማንነት የገለጠ ነው።
የሰሜን ዕዝን ከጀርባ መጨፍጨፍ የሀገር ክህደትና የባንዳነት ባህሪ የወለደው ማንነት መሆኑ በግልጽ ታይቷል። ይህ አይነቱ የጥፋት ድርጊት እንዳይደገም ትልቅ ትምህርት ተወስዶበታል።
ይህን ዕለት አስበን ስንውል ሀገራችን ኢትዮጵያ ሉዓላዊነቷን እና ክብሯን ጠብቃ ሁሌም “እንደታፈራች እንድትኖር ከዘመን ዘመን ተከብራ” በዱር በገደሉ መስዋዕትነትን የከፈሉ የሠራዊቱ አባላትን እያሰብን ነው።