“አሰብ የማን ናት?”
አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 23፣ 2019 (ኤፍ ኤም ሲ) የኢትዮጵያ የባህር በር ጥያቄ ታሪካዊ በደል እና የህልውና አጀንዳን አብሮ የያዘ የሀገራችን ፖለቲካ ምህዳር ውስጥ የቁጭት ምንጭ የሆነ ምዕራፍ ነው።
በዚህ ወሳኝ ርዕሰ ጉዳይ ላይ ጥልቅ የሆነ ሕጋዊ እና ታሪካዊ ዳሰሳ ከሚያደርጉ ሥራዎች መካከል በታዋቂው ሕግ ባለሙያ በያዕቆብ ኃይለማርያም (ዶ/ር) «አሰብ የማን ናት?» በሚል ርዕስ የተዘጋጀው መጽሐፍ ይጠቀሳል።
መጽሐፉ የኢትዮጵያን የባህር በር ባለቤትነት ከመጀመሪያው አንስቶ እስከ እያንዳንዱ ዘመን መስዋዕትነት ድረስ አሟጦ የያዘ ታላቅ ሰነድ ነው። ጸሐፊው ከፖለቲካ ወገንተኝነትና ጫና ገለል በማለት ምሁራዊ ድፍረትን በማሳየት የሀገራቸውን እውነት ያለማመንታት በመጽሐፋቸው አስፍረዋል።
የኢትዮጵያ እና የባህር በር ቁርኝት በተፈጥሮም ሆነ በታሪክ የማይካድ ሀቅ ቢሆንም ባለፉት ዘመናት የተከፈለው ግዙፍ የኢኮኖሚና የደም መስዋዕትነት ከዚህ እውነት ጋር ተመጣጣኝ ግምት አላገኘም።
ለአብነት ያህል በአጼ ኃይለሥላሴ ዘመነ መንግሥት ብቻ የባህር በር መሰረተ ልማቶችን ለማልማት እና ከሀገር ውስጥ ጋር ለማስተሳሰር የወጣው ወጪ እጅግ ግዙፍ ሀብት ነበር።
ይሁን እንጂ የሻዕቢያ አገዛዝ ስልጣን ከያዘ በኋላ ይህንን የጋራ ሀብትና የባህር ኃይል አቅም በማውደም ሀገሪቱን ከባህር በር ያራቀ ፖለቲካዊ ስህተት ተፈጽሟል።
በተለይም የኢህአዴግ አስተዳደር በባህር በር ዙሪያ የሰራው ታሪካዊ ጥፋት በወደብ ላይ ያለውን የባለቤትነት መብት በእጅጉ ጎድቶታል።
በአልጀርስ ስምምነትም ቢሆን የአሰብ ጉዳይ ወደ ጎን እንዲገፋ እና ኢትዮጵያ ተገቢውን ሕጋዊና ታሪካዊ ክርክር እንዳታደርግ እጇ የታሰረበት፣ የውጭ ኃይሎች ተጽዕኖ በከፍተኛ ሁኔታ የተንጸባረቀበት እና በግፍና በሴራ የዲፕሎማሲያዊ ሽንገላ እንዲዘጋ የተደረገ አሳዛኝ ምዕራፍ ነው።
የያዕቆብ (ዶ/ር) መጽሐፍ ዛሬ ላይ ሲታይ እጅግ አስገራሚ የሆነ ትንቢታዊ ገጽታን ያንጸባርቃል።
በወቅቱ የኢትዮጵያ ሕዝብ ቁጥር እያደገ ሲመጣ የጂኦግራፊ ሥራና የባህር በር ጥያቄ የህልውና ጉዳይ ሆኖ እንደሚመለስ የሀገሪቱ ሉዓላዊነት የሚገደውና የሚያስከብረው መንግሥት ሲመጣም ይህ ጥያቄ ሊቀር እንደሚገባው በግልጽ አስቀምጧል።
አሁን ላይ ታዲያ ኢትዮጵያ ውስጥ እንደነውር ይታሰብ የነበረውን የባህር በር ጥያቄ የመደመር መንግሥት የብሔራዊ አጀንዳ በማድረግ የጀመረው ሰላማዊ እና ሰጥቶ የመቀበል መርህን የተከተለ ዲፕሎማሲያዊ እንቅስቃሴ ይህንን ታሪካዊ ስብራት የሚጠግን ሁነኛ ርምጃ ነው።
ይሁን እና የታሪካዊ ጠላቶች እንቅስቃሴ ለኢትዮጵያ ፈተና ቢሆኑም የባህር በር ጥያቄ ጊዜያዊ የፖለቲካ ጩኸት ሳይሆን የሕዝቦች የዘለዓለም የህልውናና የፍትህ ጥያቄ መሆኑን ሁሉም ሊገነዘበው ይገባል።
በዮናስ ጌትነት