ኢትዮጵያ እና ቻይና ሁለገብ ወታደራዊ ትብብራቸውን የበለጠ ለማጠናከር ይሰራሉ
አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 24 ቀን 2019 ዓ.ም (ኤፍ ኤም ሲ) ኢትዮጵያ እና ቻይና የቆየውን ወታደራዊና ስትራቴጂካዊ ትብብራቸውን የበለጠ ለማጠናከር በትኩረት እንደሚሠሩ አረጋግጠዋል።
የመከላከያ ሚኒስትር መሐመድ እድሪስ በዛሬው ዕለት በኢትዮጵያ የቻይና አምባሳደር ቼን ሃይን በጽሕፈት ቤታቸው ተቀብለው አነጋግረዋል።
በውይይቱም ሁለቱ ሀገራት የቆየውን ወታደራዊና ስትራቴጂካዊ ትብብራቸውን ወደ ላቀ ደረጃ ለማሸጋገር በትኩረት እንደሚሠሩ አረጋግጠዋል።
ሚኒስትሩ ኢትዮጵያና ቻይና በብዙ መስኮች ፍሬያማ አጋርነት እንዳላቸው ጠቁመው፤ በተለይም በወታደራዊ ኢንዱስትሪ፣ በቴክኖሎጂ ሽግግርና በሥልጠና ዘርፍ ያለውን ትብብር ይበልጥ ማሳደግ እንደሚገባ አስምረውበታል።
አክለውም ኢትዮጵያ ብሔራዊ ጥቅሟን ለማስከበር የምታደርገው ፍትሐዊ ጥረት ለቀጣናውና ለዓለም አቀፍ ሰላም አዎንታዊ አስተዋፅኦ እንዳለው አንስተዋል።
በኢትዮጵያ የቻይና አምባሳደር ቼን ሃይ በበኩላቸው ሀገራቸው ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን ወታደራዊና ስትራቴጂካዊ አጋርነት ለማሳደግ ከፍተኛ ፍላጎት አላት ማለታቸውን የመከላከያ ኦንላይን ሚዲያ ለፋና ዲጂታል የላከው መረጃ ያመላክታል።
በተለይም በመከላከያ ኢንዱስትሪና በኢንቨስትመንት ዘርፍ የተመዘገቡ ውጤቶችን አጠናክሮ ለማስቀጠል ቻይና ዝግጁ መሆኗን አረጋግጠዋል።