የፖለቲካ አመራሮች ወታደራዊ ስልጠና መውሰዳቸው የአመራር ብቃትን ያጎለብታል- ጄኔራል ይመር መኮነን
አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 26፣ 2019 (ኤፍ ኤም ሲ) የፖለቲካ አመራሮች የወታደራዊ ሳይንስና ጥበብ ስልጠና መውሰዳቸው የአመራር ብቃትን ያጎለብታል አሉ የመከላከያ ትምህርትና ስልጠና ዋና መምሪያ ኃላፊ ጄኔራል ይመር መኮነን፡፡
ከፍተኛ የመንግሥት አመራሮች በሁርሶ ዕጩ መኮንኖች ማሰልጠኛ ትምህርት ቤት ሲወስዱ የቆዩትን የወታደራዊ ሳይንስና ጥበብ ስልጠና አጠናቅቀዋል፡፡
በሥልጠናው ማጠቃለያ ስነ-ስርዓት ላይ የተገኙት የመከላከያ ትምህርትና ስልጠና ዋና መምሪያ ኃላፊ ጄኔራል ይመር መኮነን ባስተላለፉት መልዕክት፤ ከፍተኛ አመራሮች የወታደራዊ ሳይንስ ጥበብን በመማርና በመሠልጠን የመከላከያ ሠራዊቱን የሥራ ባህል፣ ዲሲፕሊን እና መርሆዎች እንዲያውቁ የሚያግዝ መሆኑን ገልጸዋል።
ሥልጠናው ከአካላዊና አእምሯዊ ዝግጁነት፣ ከቡድን ሥራ እንዲሁም ከስትራቴጂካዊ አመራር ጋር በተያያዙ ጉዳዮች ዙሪያ ተግባራዊና ንድፈ ሃሳባዊ እውቀት ለማዳበር ያለመ መሆኑነ ገልጸዋል፡፡
በሲቪል አመራርና በመከላከያ ተቋም መካከል የጋራ ግንዛቤን ለማጠናከር የሚያግዝ እንደሆነም አመልክተዋል፡፡
ከፍተኛ አመራሮቹ የወታደራዊ ሳይንስ ስልጠና መውሰዳቸው ሀገርን ወደ ተሻለ የዕድገት ጎደና ለማሻገር የሚያግዝ ነው ብለዋል፡፡
አመራሮቹ ከነበራቸው የሥራ ባህል በተጨማሪ የወታደራዊ የሥራ ባህልና ሀገር ወዳድነትን እንዲሁም እየሞቱ ሀገርን የማፅናት የውትድርና ሙያን ለመገንዘብ እንደሚረዳም አንስተዋል።
አመራሮቹ በስልጠናው ያገኙት ተሞክሮ የመከላከያ ሠራዊቱን ተግባርና ኃላፊነት በተሻለ ሁኔታ ለመረዳት እንዲሁም በሀገራዊ ጉዳዮች ላይ የተቀናጀ አመራር ለማጠናከር እንደሚያግዝም ተናግረዋል፡፡
በሁርሶ የዕጩ መኮንኖች ማሰልጠኛ ትምህርት ቤት ለከፍተኛ የሀገሪቱ አመራሮች የተሰጠው ስልጠና የተቋሙን የማሠልጠን አቅምና ልምድ ያሳየ ተሞክሮ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
የከፍተኛ አመራሮች ሥልጠና የወታደራዊ እውቀትን፣ የአመራር ብቃትንና የሀገራዊ ርዕይ ትስስርን ለማጉላት ያለው ፋይዳ ከፍተኛ ነው ሲሉም አስረድተዋል፡፡
የሥልጠናውን ሪፖርት ያቀረቡት የሁርሶ ዕጩ መኮንኖች ማሠልጠኛ ትምህርት ቤት አዛዥ ኮሎኔል ከድር በበኩላቸው ጫጮ ከፍተኛ አመራሮቹ በተግባርና በንድፈ ሃሳብ የተከታተሉትን ስልጠና የሲቪል አመራሩ እና መከላከያ በጋራ የሀገርን ርዕይ ማሳካት የሚችሉበት ነው ብለዋል፡፡
ስልጠናው የሃገርን ብሄራዊ ጥቅም ለማስጠበቅና የደህንነት ጉዳዮችን በተቀናጀ አመራር ለመምራት የሚያስችል የጋራ ግንዛቤ የፈጠረ ነው ማለታቸውን የመከላከያ ኦንላይን ሚዲያ ለፋና ዲጂታል የላከው መረጃ ያመላክታል።