Fana: At a Speed of Life!

የሻዕቢያ የቀውስ መንገድ

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 24፣ 2019 (ኤፍ ኤም ሲ) በኢሳያስ አፈወርቂ የሚመራው የኤርትራ አገዛዝ ላለፉት ሶስት አስርት ዓመታት እየተከተለ ያለው ፖሊሲ ሀገሪቱን ለከፍተኛ የውስጥ ውጥረት እና ለቀጣናዊ መገለል ዳርጓታል።
ገደብ የሌለው ወታደራዊ አገልግሎት፣ የሕገ-መንግሥታዊ አስተዳደር እጦት፣ ኢኮኖሚያዊ ድቀት እና የዜጎች መሠረታዊ መብቶች መገደብ በሺዎች የሚቆጠሩ የኤርትራ ወጣቶች ከሀገራቸው እንዲሰደዱ ምክንያት ሆኗል።
ይህም የሀገሪቱን የሰው ኃይል እና የልማት ዕድል በእጅጉ አዳክሞታል። ኤርትራን “አፍሪካዊ ሲንጋፖር” አደርጋታለሁ ያለው ሻዕቢያ ሀገሪቱን ለህዝቧ ሲኦል የሆነች ወታደራዊ እስር ቤት አድርጓታል፡፡
በምስራቅ አፍሪካ እና በቀይ ባሕር ቀጣናም፣ ሀገሪቱ “ነጻነቷን” ባወጀች ማግስት የኢሳያስ አስተዳደር ከኢትዮጵያ፣ ጅቡቲ፣ ከየመን እና ሱዳን ጋር ወደ ግጭት በመግባት ገና በጠዋቱ የማበጣበጥ ተግባር ውስጥ ገብቷል፡፡
ከዚያ ጀምሮ በተለያየ ጊዜ በለኮሳቸው ወታደራዊ ግጭቶች የቀጣናውን ሰላም እና ኢኮኖሚያዊ ትስስር አደጋ ላይ ጥሎታል፡፡
የኢሳያስ አገዛዝ ኢትዮጵያን ሰላም ለማሳጣት ለውስጥ ባንዳዎች ድጋፍ በማድረግ ግልፅ የጸብ አጫሪነት ተግባር ከመፈጸም ወደኋላ ብሎ አያውቅም፡፡
ሻዕቢያ በጎረቤት ሀገራት ውስጣዊ ጉዳይ ጣልቃ በመግባት የአገዛዙን ውድቀቶች እና የሕዝብን የዲሞክራሲ ጥያቄዎች ለማድበስበስ እንደ ሽፋን ሲጠቀምበት ቆይቷል፤ አሁንም እየተጠቀመ ነው፡፡
ከ35 ዓመታት በላይ የቆየው አገዛዙ ግልጽ የስልጣን ሽግግር ማዕቀፍ፣ ተቋማት እና ህገ-መንግስታዊ መመሪያ የሌለው በመሆኑ፣ ከኢሳያስ አፈወርቂ በኋላ የሚፈጠረው የፖለቲካ ክፍተት ለኤርትራም ሆነ ለጠቅላላው የአፍሪካ ቀንድ ከፍተኛ የደህንነት እና የፖለቲካ አለመረጋጋት ስጋት ይዞ ይመጣል።
የኤርትራ ህዝብ ይህን ቆሞ ቀር አስተሳሰብ የተጸናወተውን ግለሰብ እና ቡድን ለመገርሰስ በቁርጠኝነት መታገል ጀምሯል፡፡ ይህን ማሳካት ከጎረቤት ሀገራት ህዝብ ጋር አብሮ የማደግና በሰላም የመኖር ዕድል ይፈጥራል፡፡
ከፋና ሚዲያ ኮርፖሬሽን ጋር ቆይታ የነበራቸው የሰማያዊ ማዕበል ፓርቲ አባላትም የሚያረጋግጡት ይህንን እውነታ ነው።
በቴዎድሮስ ሳህለ
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.