Fana: At a Speed of Life!

የመኖሪያ ቤት እጥረትን ለመቅረፍ እየተወሰዱ የሚገኙ ተጨባጭ እርምጃዎች

አዲስ አበባ፣ ሕዳር 4፣ 2019 (ኤፍ ኤም ሲ) በፍጥነት እያደጉ ባሉ የኢትዮጵያ ከተሞች፣ በተለይም በአዲስ አበባ፣ ደረጃውን የጠበቀና ተመጣጣኝ ዋጋ ያለው መኖሪያ ቤት ማግኘት ለነዋሪዎች ትልቅ ፈተና ነው።

የመደመር መንግሥትም የመኖሪያ ቤት ችግር ሕዝቡ ላይ እያደረሰ ያለውን ተደራራቢ ጫና እና ስጋት በመረዳት ለቤት ልማት ትኩረት ሰጥቷል።

በዚህም መሠረት ከጉባ ብስራቶች አንዱ በሆነው የመኖሪያ ቤት ልማት በሀገር አቀፍ ደረጃ በአምስት ዓመታት ውስጥ 1 ነጥብ 5 ሚሊየን ቤቶችን ገንብቶ ለሕዝብ ለማስረከብ ቃል በመግባት፣ ቃሉን በተግባር ለማረጋገጥ እየሠራ ይገኛል።

የሕዝቡን የመኖሪያ ቤት ሸክም ለማቃለልና ተጨባጭ ውጤት ለማስመዝገብ እየተወሰዱ ከሚገኙ ዋና ዋና እርምጃዎች መካከልም መንግሥት ባጸደቀው የመኖሪያ ቤት ፖሊሲ አማካኝነት ተመጣጣኝ ዋጋ ያላቸው መኖሪያ ቤቶችን መገንባት ይገኝበታል።

ይህም በከተሞች መስፋፋት እና በሕዝብ ቁጥር ዕድገት ምክንያት የተፈጠረውን ከፍተኛ የመኖሪያ ቤት እጥረት ለመቅረፍ ያለመ ነው። በአንድ ጊዜ ከፍተኛ ገንዘብ ከፍለው ቤት መግዛት ለማይችሉ ዝቅተኛና መካከለኛ ገቢ ላላቸው ዜጎች በመንግሥት የሚደገፍ የረጅም ጊዜ የቤት ብድር ሥርዓት ተዘርግቷል።

ይህ አሠራር ባንኮች የረጅም ጊዜ ካፒታል እንዲያገኙ በማስቻል የወር ደመወዝተኛ የሆኑ ዝቅተኛ ገቢ ያላቸው ዜጎች በተመጣጣኝ ወርሃዊ ክፍያ የራሳቸው ቤት ባለቤት እንዲሆኑ ዕድል ይፈጥራል።

ይህም የመኖሪያ ቤት ፍላጎትን በመንግሥት በጀት ብቻ ማሟላት ከባድ በመሆኑ፣ ዘርፉ ለግል አልሚዎች እና ለመንግሥትና የግል አጋርነት ሞዴሎች ክፍት እንዲሆን በማድረግ የመንግሥትን የመሬትና የፖሊሲ ድጋፍ ከግሉ ዘርፍ ካፒታልና የግንባታ ቅልጥፍና ጋር በማቀናጀት ቤቶችን በፍጥነት ለማቅረብ የሚያግዝ አሠራር ነው።

በዛሬው ዕለትም ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በአዲስ አበባ በ21 ሳይቶች እየተገነቡ የሚገኙ 100 ሺህ ቤቶችን የግንባታ ሂደት ጎብኝተዋል።

እነዚህ ፕሮጀክቶችም 50 ሺህ ቤቶች በከተማው በጀት፣ 50 ሺህ ቤቶች ደግሞ በመንግሥትና የግል አጋርነት እንዲሁም በማኅበራት ወጪ የሚገነቡ ናቸው።

የመኖሪያ ቤት እጥረትን ለመቅረፍ እየተወሰዱ በሚገኙ እርምጃዎች ወጪ ቆጣቢና ዘመናዊ የግንባታ ቴክኖሎጂዎችን መጠቀምም ሌላው መንግሥት የዜጎችን የቤት ጥያቄ ለመመለስ እያሳየ የሚገኘው ቁርጠኝነት ማሳያ ነው።

ተገጣጣሚ ቤቶችንና በሀገር ውስጥ የሚመረቱ የግንባታ ግብዓቶችን የመጠቀም ልምድ ተጠናክሯል።

ከዚህ ጎን ለጎን እየተካሄዱ ያሉ የከተማ ማደስና የኮሪደር ልማት ሥራዎች የውኃ፣ የመብራት እና የፍሳሽ ማስወገጃ መሠረተ ልማቶችን በማሻሻል ዜጎች ደረጃውን በጠበቀ የመኖርያ አካባቢ መኖር እንዲችሉ እያደረጉ ነው።

በአምስት ዓመታት ውስጥ 1 ነጥብ 5 ሚሊየን ቤቶችን ገንብቶ ማስረከብ ትልቅ ቁርጠኝነትን የሚጠይቅ ግብ ሲሆን፤ የግንባታው ፍጥነት፣ እንዲሁም ዝቅተኛና መካከለኛ ገቢ ላላቸው ዜጎች የቤቶቹ ዋጋ ተመጣጣኝ መሆን፣ ለነዋሪዎች የማስተላለፍ ፍትሐዊ ሂደት እና አካታች ተደራሽነት የፕሮጀክቱ ስኬት መለኪያዎች ናቸው።

የመደመር መንግሥት ሰፊ የመኖሪያ ቤት ግንባታ ዕቅዶችን ከፋይናንስ ማሻሻያዎችና ከግሉ ዘርፍ ተሳትፎ ጋር አጣምሮ መያዙ፣ የሕዝቡን የመኖሪያ ቤት ችግር ለማቃለልና ለዜጎች የተሻለ የኑሮ ምዕራፍ ለመክፈት ተስፋ ሰጪ መሠረት እየጣለ ይገኛል።

#ኢትዮጵያ #ትልቅሀገር #ትልቅሕዝብ #ታላቅርዕይ

በምህረት ደምሴ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.