ጠንካራ ኅብረብሔራዊ አንድነት እንዲገነባ በትኩረት እየተሠራ ነው – አቶ ደስታ ሌዳሞ
አዲስ አበባ፣ ሕዳር 3፣ 2019 (ኤፍ ኤም ሲ) ጠንካራ ኅብረብሔራዊ አንድነት እንዲገነባና ሀገራዊ ማንነት ስር እንዲሰድ በትኩረት እየተሠራ ነው አሉ የፌዴሬሽን ምክር ቤት ምክትል አፈጉባኤ ደስታ ሌዳሞ፡፡
የ21ኛው የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች በዓልን በማስመልከት በኢፌዲሪ ፌዴሬሽን ምክር ቤት ለክልሎችና ከተማ አስተዳደሮች ኮሙዩኒኬሽን ቢሮ ኃላፊዎች፣ ለሚዲያ ተቋማት ኃላፊዎችና ባለሙያዎች ስልጠና እየተሰጠ ይገኛል፡፡
ምክትል አፈ ጉባኤው በዚሁ ወቅት እንዳሉት፤ በዓሉ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች እንዲቀራረቡ፣ ብዝኃነትን በማክበር ጠንካራ ኅብረብሔራዊ አንድነት ስር እንዲሰድ ለማድረግ ያለመ ነው፡፡
መገናኛ ብዙሃን በሀገረ መንግሥት ግንባታ ሂደት ያላቸው ሚና ከፍተኛ መሆኑን ገልጸው፤ የሚዲያ ባለሙያዎች ይህንኑ ሚናቸውን ለመወጣት በተነሳሽነት መስራት እንዳለባቸው አስገንዝበዋል፡፡
የአስተናጋጁ ክልል ባሕላዊ እሴቶችና ተፈጥሯዊ ጸጋዎችን በማስተዋወቅ ሙያዊ ኃላፊነታቸውን እንዲወጡ መልዕክት አስተላልፈዋል።
21ኛው የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀን በዓል “በብዝኃነት የደመቀች፣ በምክክር የጸናች ሥልጡን ኢትዮጵያ” በሚል መሪ ሀሳብ በጅማ ከተማ ይከበራል።
በስልጠና መድረኩ ላይ በዘንድሮው በዓል መሪ ሀሳብ ላይ መነሻ ጽሑፍ ቀርቦ ውይይት እየተደረገበት መሆኑን የምክር ቤቱ መረጃ ያመለክታል፡፡
#ኢትዮጵያ #ትልቅሀገር #ትልቅሕዝብ #ታላቅርዕይ