Fana: At a Speed of Life!

የኮይሻ ኃይል ማመንጫ ፕሮጀክት የግንባታ አፈጻጸም 78 ነጥብ 3 በመቶ ደርሷል

አዲስ አበባ፣ ሕዳር 4፣ 2019 (ኤፍ ኤም ሲ) የኮይሻ ኃይል ማመንጫ ግድብ ግንባታ አፈጻጸም 78 ነጥብ 36 በመቶ ደርሷል አለ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል፡፡

ተቋሙ የ2019 በጀት ዓመት የመጀመሪያ ሩብ ዓመት እቅድ አፈጻጸም ግምገማ አካሂዷል፡፡

በሦስት ወራት ለመሙላት ከታቀደው 255 ሺህ ሜትር ኪዩብ የአርሲሲ ኮንክሪት ሙሌት ውስጥ 250 ሺህ ሜትር ኪዩብ መከናወኑ በግምገማ መድረኩ ላይ ተመላክቷል፡፡

በዚህም ከአጠቃላዩ 6 ነጥብ 4 ሚሊየን ሜትር ኪዩብ የአርሲሲ ኮንክሪት ሙሌት 82 ነጥብ 29 በመቶ ያህሉ መሞላቱ ነው የተገለጸው፡፡

ግድቡ ሲጠናቀቅ ከሚኖረው የ201 ነጥብ 5 ሜትር ቁመት ውስጥ በአሁኑ ወቅት የግድቡ የግራ ክንፍ 145 ሜትር እንዲሁም የቀሪ ክፍሎቹ አማካይ ቁመት 138 ሜትር ደርሷል።

የስድስት ተርባይኖች የኤሌክትሮሜካኒካል ሥራዎች ዕቃዎች ግዥ፣ የማጓጓዝ፣ የመገጣጠምና የተከላ ሥራዎች በዕቅዱ መሠረት እየተከናወነ መሆኑም ተመላክቷል፡፡

የግድብ ውኃ ማስተንፈሻና ማስተላለፊያ ቱቦዎች ግዥ፣ የማምረት፣ እቃዎችን የማጓጓዝ፣ የመገጣጠምና የተከላ ሥራዎችም እየተከናወኑ እንደሚገኙ ተቋሙ ገልጿል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.