ቻይና በኢትዮጵያ ኢንዱስትሪ ፓርኮች ያላትን ኢንቨስትመንት በእጥፍ ለማሳደግ እየተሰራ ነው
አዲስ አበባ፣ ሕዳር 6፣ 2019 (ኤፍ ኤም ሲ) ቻይና በኢትዮጵያ ኢንዱስትሪ ፓርኮች ያላትን ኢንቨስትመንት በሚቀጥሉት ሁለት ዓመታት በእጥፍ ለማሳደግ እየተሰራ ነው አለ የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን፡፡
የኮርፖሬሽኑ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ፍጹም ከተማ በፓርኮቹ የቻይናን ኢንቨስትመንት ማሳደግ በሚቻልባቸው ጥረቶች ዙሪያ ከሀገሪቱ አምባሳደር ቼን ሃይ ጋር ተወያይተዋል፡፡
በውይይታቸውም የሁለቱን ተቋማት ትብብር ለማጠናከርና የኢትዮጵያን የኢንዱስትሪ ኢንቨስትመንት ተወዳዳሪነት ለማሳደግ በሚያስችሉ ጉዳዮች ላይ መክረዋል፡፡
አቶ ፍጹም ከተማ በዚሁ ወቅት በኮርፖሬሽኑ በሚተዳደሩ ተቋማት ውስጥ ከሚገኙ ባለሀብቶች መካከል 200 የሚጠጉት ማምረት መጀመራቸውንና 43ቱ የቻይና ኩባንያዎች መሆናቸውን ተናግረዋል።
ኮርፖሬሽኑ በአሁኑ ወቅት 14 ልዩ ኢኮኖሚ ዞኖችንና ኢንዱስትሪ ፓርኮችን እያስተዳደረ ሲሆን፤ ከ300 በላይ የሀገር ውስጥና የውጭ ባለሀብቶችን በማስተናገድ ከ100 ሺህ በላይ የሥራ ዕድሎችን መፍጠሩን አስረድተዋል።
አምባሳደር ቼን ሃይ በበኩላቸው፤ በኢንዱስትሪ ፓርኮችና ልዩ ኢኮኖሚ ዞኖች የቻይናን ኢንቨስትመንት በሚቀጥሉት ሁለት ዓመታት በእጥፍ ለማሳደግ የሚደረጉ ጥረቶችን እንደሚደግፉ አረጋግጠዋል፡፡
አዳዲስ የቻይና የንግድ ልዑካን ቡድኖችን ከኮርፖሬሽኑ ጋር ለማገናኘት እንደሚሠሩ መናገራቸውን ከኮርፖሬሽኑ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡
ሁለቱ ወገኖች ተቋማዊ ትብብራቸውን ለማጠናከርና የኢትዮጵያን ኢንዱስትሪያላይዜሽን ሂደት ለማሳደግ ቁርጠኛ መሆናቸውን አረጋግጠዋል።
#ኢትዮጵያ #ትልቅሀገር #ትልቅሕዝብ #ታላቅርዕይ