Fana: At a Speed of Life!

15ኛው ዓለም አቀፍ የጥራጥሬና ቅባት እህሎች ኮንፈረንስ በአዲስ አበባ ሊካሄድ ነው

አዲስ አበባ፣ ሕዳር 8፣ 2019 (ኤፍ ኤም ሲ) 15ኛው ዓለም አቀፍ የጥራጥሬና ቅባት እህሎች ኮንፈረንስ በመጪው ሕዳር 15 እና 16 በአዲስ አበባ ሳይንስ ሙዚየም ይካሄዳል፡፡

የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስትር ወ/ሮ ያስሚን ወሀብረቢ እና የኢትዮጵያ ጥራጥሬና ቅባት እህሎች ላኪዎች ማህበር ፕሬዚዳንት አቶ ኢደኦ አብዲ ኮንፈረንሱን አስመልክተው መግለጫ ሰጥተዋል፡፡

“የማይበገር ንግድና ዘላቂ የእሴት ሰንሰለቶች” በሚል መሪ ሀሳብ በሚካሄደው ኮንፈረንስ ላይ ከ17 ሀገራት የተውጣጡ ከ600 በላይ አምራቾች፣ ላኪዎች፣ ዓለም አቀፍ ገዢዎች፣ የፋይናንስ ተቋማት፣ አምባሳደሮችና የመንግሥት ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች ይሳተፋሉ፡፡

በኮንፈረንሱ የፖሊሲና የዓለም አቀፍ ገበያ አዝማሚያ፣ የገበያ መዳረሻዎች፣ የምርት ጥራት መስፈርቶች፣ በዘርፉ እያጋጠሙ ባሉ ተግዳሮቶችና ሌሎች ተያያዥ ጉዳዮች ዙሪያ ከ15 በላይ ጥናታዊ ጽሑፎች ቀርበው ውይይት እንደሚደረግባቸው ሚኒስትሯ ገልጸዋል።

በመደመር መንግሥት ሀገር በቀል የኢኮኖሚ ፖሊሲና የማክሮ ኢኮኖሚ ሪፎርም የወጪና ገቢ ንግዳችን የላቀ አፈጻጸም እያስመዘገበ ነው ያሉት ሚኒስትሯ፤ ባለፉት አራት ወራትም ይኸው አፈጻጸም ተጠናክሮ መቀጠሉን አንስተዋል።

ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ፣ ምርት ወደ ገበያ እንዲወጣና ለዓለም ገበያ እንዲቀርብ ክትትል ለማድረግ፣ የምርት ጥራትን ለማስጠበቅ እንዲሁም አጠቃላይ የንግድ ዘርፉን አገልግሎት አሰጣጥ ለማዘመን ሰፊ ሥራ መሰራቱን አብራርተዋል።
አቶ ኢደኦ አብዲ በበኩላቸው፤ እንደ ሀገር ያለንን እምቅ አቅም ተጠቅመን ያመረትነውን በዓለም አቀፉ ገበያ ለመሸጥ ዓለም አቀፉን የገበያ ፍላጎት ማወቅና መገመት የሚያስችል አቅም መፍጠር ይገባል ብለዋል፡፡

ኮንፈረንሱ የገበያ አዝማሚያን ለመረዳት፣ ምርትን ለማስተዋወቅ እንዲሁም በገዢዎችና ሻጮች መካከል የተጠናከረ የመረጃ ፍሰት እንዲኖር ያግዛል ነው ያሉት፡፡

በተካልኝ ኃይሉ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.