የኢትዮጵያ የዘመኑ ሉዓላዊነት በምግብ ራስን በመቻልና በዲጂታል አቅም ይረጋገጣል – አቶ አደም ፋራህ
አዲስ አበባ፣ ሕዳር 8፣ 2019 (ኤፍ ኤም ሲ) የኢትዮጵያ የዘመኑ ሉዓላዊነት በምግብ ራስን በመቻልና በዲጂታል አቅም ይረጋገጣል አሉ የብልጽግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዚዳንት አቶ አደም ፋራህ።
ዘመናዊ የእጅ አዙር ቅኝ ግዛትን ለመታገል የተቋቋመው “ለሕዝቦች ነፃነት” ዓለም አቀፍ ንቅናቄ ጠቅላላ ጉባዔ በሩሲያ ሞስኮ እየተካሄደ ነው።
በብልጽግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዚዳንት አቶ አደም ፋራህ የተመራ ከፍተኛ የልዑካን ቡድን በጉባኤው ላይ እየተሳተፈ ይገኛል።
አቶ አደም ፋራህ በጉባኤው ላይ ኢትዮጵያ በብሔራዊ ሉዓላዊነት፣ በልማት የራስን በራስ የመወሰን ነፃነት እና እየተለዋወጠ በመጣው የዓለም አቀፍ ግንኙነት ሥርዓት ዙሪያ ያላትን አቋምና ምልከታ አቅርበዋል።
ኢትዮጵያ ለብሔራዊ ሉዓላዊነት፣ ለሀገራት እኩል ክብር እንዲሁም በተባበሩት መንግሥታት ቻርተርና በዓለም አቀፍ ሕግ ላይ ለተመሠረተ ፍትሐዊ ዓለም አቀፍ ሥርዓት ያላትን ጽኑ ቁርጠኝነት አረጋግጠዋል።
በዓድዋ ድል ኢትዮጵያ የቅኝ ግዛትን በመመከት እና የሕዝቦችን ነፃነትና የራስን ዕድል በራስ የመወሰን መብት በማስከበር ረገድ ያላትን የቆየ ታሪካዊ ቅርስ አስታውሰዋል።
የዘመኑ ሉዓላዊነት አዳዲስ ወቅታዊ ፈተናዎችን መቋቋምን ያጠይቃል ያሉት ፕሬዚዳንቱ በዚህ ረገድ ኢትዮጵያ በምግብ ራስን በመቻል፣ በዲጂታልና በመረጃ አስተዳደር፣ በሳይበር ደኅንነት፣ በኢኮኖሚ ብዝኃነት እና በተቋማዊ ማሻሻያዎች አማካኝነት ስትራቴጂካዊ ነፃነቷን ለማጠናከር እየሰራች እንደምትገኝ አመልክተዋል።
በተጨማሪም ሀገሪቱ ሀብቷንና አቅሟን በማስተባበር ዘላቂና በራስ አቅም ላይ የተመሠረተ ልማት ለማረጋገጥ ያላትን ቁርጠኝነት የሚያሳዩ ግዙፍ ሀገራዊ ኢኒሼቲቮች እየተገበረች ይገኛል ነው ያሉት።
የአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ-ግብርን፣ የስንዴ ልማትን፣ የከተማ ኮሪደር ልማትን እና ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብን በማሳያነት ጠቅሰዋል።
ከዚህም ባሻገር ውጤታማ የባለብዙ ወገን ትብብር በዓለም አቀፍ ተቋማት ውስጥ የአፍሪካ ፍትሐዊ ውክልና መረጋገጥ፣ የጋራ ተጠቃሚነትን መሠረት ያደረጉ ዓለም አቀፍ አጋርነቶች እንዲሁም ሰላምና እርቅ ለጋራ ብልጽግና መሠረት መሆናቸውን አስገንዝበዋል።
በጉባዔው ውይይቶች፣ የክብ ጠረጴዛ ምክክሮች እና የሁለትዮሽ ንግግሮች እየተደረጉ ሲሆን፤ በማጠቃለያውም የውሳኔ ሐሳቦችና ስትራቴጂካዊ የሁለትዮሽ ስምምነቶች ይፈረማሉ ተብሎ ይጠበቃል።
ብልጽግና ፓርቲ የፖለቲካ ምክክሮችን ወደ ተጨባጭ ዓለም አቀፍ ትብብር ለመቀየር የኢትዮጵያን ታሪካዊ ቅርስና ወቅታዊ የልማት ተሞክሮ ለማስተዋወቅ እንዲሁም እየተለዋወጠ ባለው ዓለም አቀፍ ሥርዓት ውስጥ የሀገሪቱን ስትራቴጂካዊ ጥቅሞች ለማስከበር እንደሚሰራም ተገልጿል።