በአራት ወራት 2 ሺህ 472 ኪ.ሜ የኤሌክትሪክ መስመር ግንባታና ማስፋፊያ ሥራ ተከናወነ
አዲስ አበባ፣ ሕዳር 10፣ 2019 (ኤፍ ኤም ሲ) በአራት ወራት ውስጥ 2 ሺህ 472 ኪ.ሜ የኤሌክትሪክ መስመር የመልሶ ግንባታና የማስፋፊያ ሥራ ተከናኗል አለ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት።
አገልግሎቱ ለፋና ዲጂታል በላከው መረጃ፤ በነባር መስመሮች የመልሶ ግንባታና የማሻሻያ ሥራ 749 ኪ.ሜ መካከለኛ መስመር እና 82 ኪ.ሜ ዝቅተኛ መስመር፣ በድምሩ 831 ኪ.ሜ ሥራ ማከናወን መቻሉን ገልጿል።
ከአቅማቸው በላይ በጭነት ምክንያት የአገልግሎት መቆራረጥ ሊያስከትሉ የሚችሉ 481 ትራንስፎርመሮች ከፍተኛ አቅም ባላቸው ትራንስፎርመሮች መተካታቸውን እንዲሁም ተጨማሪ 411 ትራንስፎርመሮች መተከላቸውን አመልክቷል።
የኤሌክትሪክ አገልግሎት ሽፋንን ለማስፋፋት በተከናወነው ሥራ ደግሞ 978 ኪ.ሜ መካከለኛ መስመር እና 662 ኪ.ሜ ዝቅተኛ መስመር፣ በድምሩ 1 ሺህ 640 ኪ.ሜ አዲስ መስመር መዘርጋቱን የገለጸው አገልግሎቱ በእነዚህ የማስፋፊያ ሥራዎች 1 ሺህ 744 ትራንስፎርመሮችም ተከላ መትከላውቸን ነው ያብራራው።
እነዚህ ሥራዎች በተቋሙ የውስጥ ፋይናንስ ብቻ መከናወናቸውን አገልግሎቱ የነባር መስመሮችን ጥራትና አቅም ለማሻሻል፣ የኤሌክትሪክ ሽፋንን ለማስፋፋት እንዲሁም የአገልግሎቱን ተደራሽነትና ቀጣይነት ለማጠናከር ያለውን ቁርጠኝነት የሚያሳይ መሆኑን ገልጿል።
የተከናወኑት የመልሶ ግንባታና የማስፋፊያ ሥራዎች የኤሌክትሪክ አቅርቦትን ለማጠናከር፣ የአገልግሎት ጥራትን ለማሻሻል እና የኢንዱስትሪ፣ የንግድ፣ የግብርናና የማኅበራዊ አገልግሎቶችን ዕድገት ለመደገፍ ጉልህ አስተዋጽኦ እንደሚያበረክቱም አመልክቷል።
#ኢትዮጵያ #ትልቅሀገር #ትልቅሕዝብ #ታላቅርዕይ