በላሊበላ ከተማ የዓለም እጽዋት የማደጎ ዛፍ ፕሮጀክት የችግኝ ተከላ ተከናወነ
አዲስ አበባ፣ ጳጉሜን 2፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) በላሊበላ ከተማ የዓለም እጽዋት የማደጎ ዛፍ ፕሮጀክት የችግኝ ተከላ ተካሄደ።
መርሃ ግብሩን አስመልክቶ ለመገናኛ ብዙሃን መግለጫ የሰጡት የባህልና ቱሪዝም ሚንስትሯ ዶክተር ሂሩት ካሳው መርሃ ግብሩ በአገር ውስጥ ቱሪዝም መነሻ ስፍራ በላሊበላ ቢጀመርም በመላው ኢትዮጵያ ለማስፋት ይስራል ብለዋል።
ዶክተር ሂሩት ፕሮጀክቱ አካባቢውን ጸጋ በመመለስ ከማስቻሉም በላይ ለከተማዋ ነዋሪዎች የስራ ዕድል መፍጠር ያስችላል ሲሉ አንስተዋል።

በዕለቱም የዓለም እጽዋት የማደጎ ዛፍ ፕሮጀክት የችግኝ ተከላ ተረካቢዎች ባሉበት ተከናውኗል።
ለዚህ ፕሮጀክትም የተለያዩ አካላት 7 ሚሊየን ብር ገደማ ለመለገስ ቃል ገብተዋል።
በቀጣይም በተለያዩ የመገናኛ አማራጮች በመጠቀም በአገር ውስጥ የሌሉ አካላትም በማደጎ የዛፍ ፕሮጀክቱ ላይ ይሳተፋሉ ሲሉ ነው የተናገሩት።
የዓለመ እጽዋት የማደጎ ዛፍ ተከላን ለፈጸሙ አካላት የምስክር ወረቀት ተበርክቷል።
የፕሮጀክቱ መሰረታዊ ዓላማም የቅዱስ ላሊበላን ቅርስ ለመጎብኝት የሚመጡ የውጪ እና የአገር ውስጥ ጎብኚዎች የአገር በቀል ችግኞች እንዲተክሉ የሚያስችል ነው።
በዚህም እንግዶች የሚተክሏቸውን ችግኞች የከተማዋ ነዋሪ በአደራ ተረክቦ የሚንከባከብበት ይሆናል ተብሏል።
በተጨማሪም ጎብኚው ለተንከባካቢው ወገን ክፍያ የሚፈጽምበት አሰራር መዘርጋቱንም ጠቅሰዋል።
ይህም በጎብኚዎች እና በአካባቢው ማህበረሰብ መካከል መቀራረብ ከመፍጠሩም በላይ የእኔነት ስሜት እንዲዳብር ያደርጋል ተብሏል።
በሌላ በኩል በወልዲያ ዩኒቨርሲቲ የቅዱስ ላሊበላ ቅርስና ቱሪዝም ተቋም የመሰረት ድንጋይ የማስቀመጥ ስነ ስርዓትም ተከናውኗል።
ዶክተር ሂሩት ካሳው ተቋሙ ቅርሶችን በመስራት ያካበትነውን እውቀት በቅርስ ጥናትና ጥገና ላይ ለማዋል ያግዛል ብለዋል።
ይህ ተቋም በዘርፉ ለሚደረግ ጥናትና ምርምር የበኩሉን ከመወጣቱም በላይ፤ በዘርፉ የሰለጠነ የሰው ኃይል ለማፍራት ያግዛልሲሉ ነው የተናገሩት።
በምስክር ስናፍቅ