Fana: At a Speed of Life!

የኮሮና ቫይረስ የመከላከል ስራን ለማጠናከርና የምርመራ አቅማቸውን ለማሳደግ እየሰሩ መሆኑን የጋምቤላና የሐረሪ ክልሎች አስታወቁ

አዲስ አበባ፣ መስከረም 5፣ 2013 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የኮሮና ቫይረስ የመከላከል ስራን ለማጠናከር እና የምርመራ አቅማቸውን ለማሳደግ እየሰሩ መሆኑን የጋምቤላ እና የሐረሪ ክልሎች አስታወቁ።

ከፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ጋር ቆይታ ያደረጉት የጋምቤላ ክልል ርእሰ መስተዳድር አቶ ኡሙድ ኡጁሉ እና የሐረሪ ክልል ርእሰ መስተዳድር አቶ ኢርዲን በድሪ፥ የኮቪድ 19 ስርጭት እየጨመረ በመሆኑ የጥንቃቄ ስራዎች ላይ በትኩረት እንሰራለን ብለዋል።

የጋምቤላ ክልል ርእሰ መስተዳድር አቶ ኡሙድ ኡጁሉ በህብረተሰቡ ያለው የግንዛቤ ሁኔታ ጥሩ ቢሆንም፤ ግንዛቤውን ወደ ተግባር መቀየር ላይ ከፍተኛ ቸልተኝነቶች ይስተዋላሉ ይላሉ።

ይህም የቫይረሱ ስርጭት እንዲሰፋ ዋነኛ ምክንያት እየሆነው ነው ብለዋል።

በሐረሪ ክልል ከ1 ሺህ 400 በላይ ሰዎች የኮሮና ቫይረስ ሲገኝባቸው፤ ከ25 በላይ ሰዎችም በቫይረሱ ሳቢያ ህይወታቸው አልፏል።

የክልሉ ርእሰ መስተዳድር አቶ ኢርዲን በድሪም፥ በክልሉ የቫይረሱ ስርጭት እየጨመረ መምጣቱን ነው የሚናገሩት።

የቫይረሱ ስርጭት እየሰፋ ቢሆንም የህብረተሰቡ ጥንቃቄ ግን አሁንም ዋጋ ሊያስከፍል የሚችል ነው ይላሉ።

በክልሉ ይህን ቸልተኝነት ለመቀልበስም በርካታ ስራዎች እየተሰሩ ሲሆን፥ በተደረገ የምርመራ ዘመቻም በክልሉ የቫይረሱ የተጋላጭነት ሁኔታ 5 በመቶ ላይ መድረሱም ታውቋል።

በተደረጉ ጥናቶችም በክልሉ በቫይረሱ ከሚያዙት ውስጥ ከ90 በመቶ በላይ የሚሆኑት ሰዎች ደግሞ ምልክት የማያሳዩ ናቸው።

ክልሎቹ የቫይረሱን ስርጭት ለመግታት የሚያስችሉ ስራዎችንም እየከወኑ መሆኑን ይገልጻሉ።

በጋምቤላ ክልል የምርመራን አቅም ከማሳደግ ጀምሮ የግንዛቤ ስራዎችን መስራትም ትኩረት ተደርጎባቸዋል።

በተለይም ከጎረቤት ሀገር ደቡብ ሱዳን ጋር የሚዋሰነው የጋምቤላ ክልል ወደ ክልሉ የሚያስገቡ 8 በሮችን በመጠቀም የሚገቡ ስደተኞችን የመመርመር እና ለይቶ የማቆየት ስራ ላይ ትኩረት አድርጓል።

በሀረሪ ክልልም ቢሆን ከጎረቤት ሀገራት የሚገቡትን ጨምሮ ከሌሎች ክልሎች የሚያዋስኑ ቦታዎች ላይ ሰፊ ስራዎች እየተሰሩ መሆኑ የቫይረሱን ስርጭት ለመግታት
የሚያግዝ እንደሚሆን ነው አቶ ኦድሪን የሚናገሩት።

በሁለቱም ክልሎች የለይቶ ማቆያ እና ማከሚያ ማእከላትን የማስፋት ስራዎችም እየተሰራ ሲሆን፥ በተያዘው ዓመት የኮቪድ 19 ስርጭት የሚያደርሰውን ጫና መቋቋም የሚያስቸሉ ስራዎችም በትኩረት ይሰራባቸዋል ነው የተባለው።

ቫይረሱ ኢኮኖሚያዊ፣ ማህበራዊ እና ፖለቲካዊ ቀውሱ የከፋ እንዳይሆን አሁን ያለውን መዘናጋት ሊቀርፉ የሚችሉ የስርጭት መጠኑን የሚቀንሱ መከላከል ላይ ያተኮሩ ስራዎች ላይ ማተኮር ቀዳሚ መፍትሄ መሆኑም በርሳነ መስተዳድሮቹ ተነስቷል።

በዙፋን ካሳሁን

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.