አምባሳደር ዶ/ር ማርቆስ ተክሌ የሹመት ደብዳቤያቸዉን ፕሬዚዳንት አብዱል ፈታህ አል ሲሲ አቀረቡ
አዲስ አበባ ፣ መስከረም 13 ፣ 2013 (ኤፍ.ቢ.ሲ) በግብፅ የኢትዮጵያ አምባሳደር ዶክተር ማርቆስ ተክሌ ሪቄ የሹመት ደብዳቤያቸዉን ለግብፅ ፕሬዚዳንት አብዱል ፈታህ አል ሲሲ አቅርበዋል፡፡
አምባሳደር ዶክተር ማርቆስ ተክሌ በዛሬው ዕለት በኢታሃዲያ ቤተመንግስት በተደረገዉ ስነ ስርአት ላይ ነው የሹመት ደብዳቤያቸዉን ያቀረቡት።
በዚህ ወቅት አምባሳደር ማርቆስ ፕሬዚዳንት አብዱል ፈታ አል ሲሲ ከኢትዮጵያ ህዝብ እና መንግስት የተላከ ሰላምታ እና መልእክት አድርሰዋል።
በመልዕክቱም ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ እና ጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ አህመድ ለፕሬዚዳንቱ መልካም ጤንነትን፤ ለግብጽ ህዝብ ደግሞ እድገትንና ብልጽግናን መመኘታቸው በግብፅ የኢትዮጵያ ኤምባሲ ያወጣው መረጃ ያመለክታል።
አምባሳደር ዶክተር ማርቆስ በግብጽ ቆይታየ የተሰጠኝ አንድ ትልቅ ሃላፊነት የሁለቱን ህዝቦች ግንኙነት ወደ ሚገባው ከፍታ መውሰድ ነው፣ ይህንን ታሪካዊ ሃላፊነት ለመወጣት ፕሬዚዳንት አብዱል ፈታህ አል ሲሲ እና መንግስታቸው ከፍተኛ ትብብር እንደሚያደረጉልኝ ተስፋዮ የጸና ነው በማለት መልዕክታቸዉን አስተላልፈዋል፡፡