ዶ/ር ኢ/ር ስለሺ በቀለ ከተመድ የአፍሪካ ኢኮኖሚ ኮሚሽን ዋና ጸሃፊ ጋር በመሆን የኮይሻ የሃይድሮ ኤሌክትሪክ ማመንጫ ግድብ ግንባታን ጎበኙ
አዲስ አበባ፣ መስከረም 24፣ 2013 (ኤፍ.ቢ.ሲ)የውሃ፣መስኖ እና ኢነርጂ ሚኒስትር ዶክተር ኢንጂነር ስለሺ በቀለ ከተመድ የአፍሪካ ኢኮኖሚ ኮሚሽን ዋና ጸሃፊ ከቬራ ሶንግዌ ጋር በመሆን የኮይሻ የሃይድሮ ኤሌክትሪክ ማመንጫ ግድብ ግንባታን ጎበኙ፡፡
ሚኒስትሩ ከተባበሩት መንግስታት ድርጀት የአፍሪካ ኢኮኖሚ ኮሚሽን ስር ዋና ጸሃፊ ከቬራ ሶንግዌ ጋር ኦሞ ወንዝ ላይ እየተገነባ የሚገኘውን የጊቤ 4 ወይም ኮይሻ የሃይድሮ ኤሌክትሪክ ማመንጫ ግድብ ግንባታን እንዲሁም ሃይል በማመንጨት ላይ የሚገኘውን የጊቤ 3 የሃይል ማመንጫን ጎብኝተዋል፡፡
ዶክተር ኢንጂነር ስለሺ በቀለ ጉብኝቱን አስመልክተው በማህበራዊ ትስስር ገፃቸው እንዳሉት ÷ይህ ጉብኝት ሃገራችን ኢትዮጵያ ያሏትን የውሃ ሃብቶች ለዘላቂ እድገትና ለዜጎች ህይወት መሻሻል እንዴት በአግባቡ እየተጠቀመች እንደሆነ ያሳያል፡፡
ጊቤ ሶስት ከ3 አመታት በፊት ግንባታው ተጠናቆ በአሁኑ ሰአት 1 ሺህ 870 ሜጋ ዋት ሃይል የማመንጨት አቅም ያለው መሆኑን ያነሱት ሚኒስትሩ አሁን ግንባታው 39 በመቶ የደረሰው ጊቤ 4 ወይን ኮይሻ ሲጠናቀቅ ደግሞ 2 ሺህ 160 ሜጋ ዋት የኤሌክትሪክ ሃይል ያመነጫል ነው ያሉት፡፡